ጥቅምት 4/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) እንደ ሀገር እድሚያቸው እስከ 14 ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሕጻናት ለከፍተኛ የአእምሮ ሕመም ተጋላጭ መሆናቸው በተለያዩ ጥናቶች ተረጋግጧል ሲሉ በጤና ሚኒስቴር የአእምሮ ጤና ፕሮግራም ባለሙያ አቶ ጀማል ተሾመ ገልጸዋል።

ለዚህ ምክንያት የሆነው ደግሞ በኢትዮጵያ አልፎ አልፎ የሚፈጠሩ ግጭቶችና ጦርነቶች፣ የአየር ንብረት መዛባት፣ የአንዳንድ የቤተሰብ ጫና ወይም ለሕጻናቶች የሚሰጡት ትኩረት ዝቅተኛ መሆን፣ ሕጻናቶች ነገሮችን በተለያዩ መልክ የመረዳት አቅማቸዉ ያልበሰለ ወይም ዝቅተኛ መሆኑ፣ ጤና ተቋማት ከላይኛው እስከታችኛው የእርከን ደረጃ በዘርፉ ላይ ተናቦና ወጥ በሆነ መንገድ አለመስራታቸው እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለዘርፉ የሚደረግ የፋይናንስ ድጋፍ አለመኖር በዋነኝነት ጠቅሰዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በበሽታው የሚጠቁት ሴቶች፣ አዛውንቶች፣ በተለያዩ ምክንያቶች የተጎዱ አቅመ ደካሞች እና በአጠቃላይ ሰወሰ ሰራሽና ተፈጥሮዊ ችግሮችን መቋቋም የማይችሉ ዜጎች ተጋላጭነታቸው ባለሙያው አስታውቀዋል።

የአይምሮ ሕመም ተጠቂዎችን መቀነስ የሚችለው ጤና ሚኒስቴር ብቻ አይደለም የሚሉት ባለሙያወሸ፤ ሁሉም ተቋማትና የዘርፉ ባለሙያዎች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የቅድመ የምክር አገልግሎት መስጠት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ይህን ችግር በአጠቃላይ መንግሥት ለመቅረፍ፤ ሕክምና የሚሰጡ ተቋማትን በክልሎች ለማስፋት እንዲሁም ሕክምናውን ተግባራዊ አድርገው እንዲሰሩ ሰፊ ትኩረት ሰጥቶት እየሰራ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር ለአሐዱ አስታውቋል።

በኢትዮጵያ 11 በመቶ የሚሆኑ ዜጎች ለአይምሮ ሕመም የተጠቁ ሲሆኑ፤ ከተጠቁት ዜጎች መካከል 30 በመቶ ለሚሆኑት የሕክምና አገልግሎት የሚሰጠው በአዲስ አበባ በሚገኙ ሆስፒታሎች መሆኑን አሐዱ ከዚህ ቀደም መዘገቡ ይታወሳል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ