ጥቅምት 13/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በትግራይ ክልል ከሚገኙ የሚድያ ባለሙያዎች ጋር ለሁለት ቀናት ያካሄደው የመጀመሪያው ዙር የውይይት መድረክ መጠናቀቁን አስታውቋል፡፡
በዚህ መድረክ ተገኝተው ስለ ኮሚሽኑ የሥራ እንቅስቃሴ ማብራሪያ የሰጡት የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን ዓርዓያ (ፕ/ር)፤ ኮሚሽኑ በ11 ክልሎች፣ በሁለት ከተማ አስተዳደሮች፣ እንዲሁም በፌደራል ተቋማትና በዳያስፖራው ማህበረሰብ አካባቢዎች አጀንዳ አሰባስቦ ማጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡
የኮሚሽኑ የቀጣይ ዋና ትኩረት የትግራይ ክልል መሆኑን ያነሱት ዋና ኮሚሽነሩ፤ ያለ ትግራይ ክልል ተሳትፎ ምክክር አካሄድን ማለት ስለማይቻል ለተግባራዊነቱ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
የክልሉ ምክክር ይሳካ ዘንድ የሚዲያ ባለሙያዎች ለሕብረሰተቡ ግንዛቤ በመፍጠር በሙያቸው እንዲያግዙም ዋና ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመጀመሪያው ዙር የውይይት መድረክ የተሳተፉ የሚዲያ ባለሙዎች በሰጡት አስተያየት፤ ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል ምክክር ለማድረግ በቅድሚያ በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት የተቀመጡ ተግባራት መፈፀም እንዳለባቸው አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡
ባለሙያዎቹ በመጠለያ ያሉ ተፈናቃዮች ወደ ቦታቸው ይመለሱ፣ የትግራይ ክልል ግዛቶች ይከበሩ የሚሉና ሎሎች በክልሉ ሕዝብ ህልውና ላይ ተጋርጠዋል ያሏቸውን የህልውና ችግሮች አንስተዋል፡፡
ኮሚሽኑ በቀጥታ እነዚህን ጥያቄዎች የመመለስ ስልጣን የሌለው መሆኑን እንደሚገነዘቡ የገለጹት የሚዲያ ባለሙያዎቹ፤ በመንግሥት ላይ ግፊት በማድረግ ግን ችግሮች እንዲፈቱ ሚና መጫወት ይችላል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ማጠቃለያ ንግግር ያደረጉት ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ/ር)፤ የትግራይ ክልል ሁኔታ በተለየ መልኩ መስተናገድ እንዳለበት እንረዳለን ብለዋል፡፡
እንደ ሀገር ችግር ውስጥ ነን ያሉት ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ፤ ትግራይ ክልል ግን በተለየ ችግር ውስጥ ስለመሆኑ ኮሚሽኑ እንደሚረዳም አክለዋል፡፡
ለሁሉም ችግር መነጋገር መፍትሄ እንደሆነ እናምናለን ያሉም ሲሆን፤ የሚዲያ ባለሙያዎች መነጋገር የሚቻልበትን ድልድይ በመፍጠር ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
የክልሉ ሕዝብ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች እንረዳለን፣ ዋጋም እንሰጣለን ሲሉም ኮሚሽር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
በማንኛውም አጋጣሚ የክልሉ ሕዝብ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በማንሳት ምክክሩን ማካሄድ የሚቻልበት አውድ እንዲፈጠር እየሰራን ነው፤ ይህንንም አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉም አፅኦት ሰጥተውበታል፡፡
ጥቅት 12 እና 13/2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተካሄደው የሁለት ቀናት የውይይት መድረክ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የግልና የዲጂታል መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እንዲሁም የማህበረሰብ አንቂና በጎ ተፅኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እንደተሳተፍበት አሐዱ ከኮሚሽኑ ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ሁለተኛው ዙር ውይይት ነገ ጥቅምት 14 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚቀጥል ተመላክቷል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
"የትግራይ ክልል ሕዝብ ጥያቄዎችን እንረዳለን፤ ዋጋም እንሰጣለን" ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን