"ምርጫ ለማድረግ አስቻይ ሁኔታ የለም" የፖለቲካ ፓርቲዎች በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሠሌዳ ውይይት ጠንካራ ተቃውሞ አሰምተዋል።
ኢትዮጵያ 7ኛውን ብሔራዊ ምርጫ ለማከናወን በወራት የሚቆጠሩ ጊዜያት ቀርተዋታል። በሀገሪቱ ባሉ አለመረጋጋቶች ምክንያት በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የፖለቲካ ሰዎች "ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ የለም" ሲሉ አጥብቀው ይከራከራሉ።
በሕገ-መንግሥቱ መሠረት በየ5 ዓመቱ ምርጫ የምታካሂደው ኢትዮጵያ፤ ያለፈውን 6ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለአንድ ዓመት ማራዘሟ ይታወሳል።
በያዝነው ዓመት በ2018 መጨረሻ እንደሚካሄድ የሚጠበቀው ምርጫም "መካሄድ አለበት" እና "መካሄድ የለበትም" በሚሉ ሁለት ሐሳቦች ተከፍሏል፡፡ ከምርጫ በፊት ያለው ውይይትም አጓጊነቱ ቀጥሏል።
ይህ በዚህ እንዳለ፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ረቂቅ የጊዜ ሠሌዳ አስመልክቶ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ምክክር ማድረጉን ገልጿል።
ቦርዱ ከረብዕ ጥቅምት 11 ጀምሮ ፓርቲዎች የክርክር የተግባር ልምምድ የሚያደርጉበትን መድረክ ያዘጋጀ ሲሆን፤ እስከ ነገ ጥቅምት 14 ድረስ እንደሚቀጥል ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በተያዘው ዓመት ለማካሄድ ልዩ ልዩ የቅድመ-ምርጫ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን አስታውቋል።
ቦርዱ ጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ.ም. የ7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ረቂቅ የጊዜ ሠሌዳ በማስመልከት ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ተወካዮች ጋር ምክክር አድርጓል።
ይህ ረቂቅ የጊዜ ሠሌዳ የምርጫ ጽሕፈት ቤቶችን ከማደራጀት ጀምሮ እስከ ይፋዊ የምርጫ ውጤት ማሳወቂያ ድረስ ያሉትን ተግባራት ያካተተ ነው።
ቦርዱ ይህንን ውይይት ከመገናኛ ብዙኃን ዝግ አድርጎታል፡፡ በቦርዱ የተመዘገቡ 60 የሚሆኑ ፓርቲዎች እንደተሳተፉበትም ተነግሯል፡፡
የአንድ ኢትዮጵያዊ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (አኢዴፓ) ሊቀመንበር አቶ ዘሪሁን ገብረእግዚአብሔር የሰኞ ዕለት ውይይት ረቂቅ የጊዜ ሠሌዳ ላይ ያተኮረ መሆኑን ተናግረዋል።

"ነገር ግን ቦርዱ ረቂቅ ነው ያቀረበው" ያሉት አቶ ዘሪሁን፣ የመጨረሻ ውሳኔ ያልተላለፈበት መሆኑን ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ፤ በውይይቱ ወቅት ከፓርቲዎች ጠንከር ያለ "በሀገሪቱ ምርጫ ለማድረግ የሚያስችል አስቻይ ሁኔታ አለመኖሩን" የሚመለከት ሀሳብ መሰንዘሩን ተናግረዋል።
ቦርዱም ለተነሱት ሀሳቦች የሰጠው ምላሽ፤ የቦርዱ ሥራ አምስት ዓመት እየጠበቁ ምርጫ ማከናወን እንደሆነ አመልክቷል። አስቻይ ሁኔታ መፍጠር ያለበት አካል ደግሞ ሌላ መሆኑን ቦርዱ ምላሽ እንደሰጠ ተገልጿል።
አቶ ዘሪሁን "እንደ አኢዴፓም በዚህ ዓመት ምርጫ ለማድረግ የሚያስችል አስቻይ ሁኔታ የለም" ሲሉም አቋማቸውን ገልጸዋል።
በውይይቱ ወቅት በሁሉም ፓርቲዎች 'ምርጫን ለማድረግ አስቻይ ሁኔታ የለም' የሚል ሐሳብ መሰንዘሩን ያነጋገርናቸው ፓርቲዎች ገልጸዋል።
ለመሆኑ 'አስቻይ ሁኔታ የለም' ከተባለ ምርጫው እንዲራዘም ወይስ ሌላ የቀረበ የመፍትሔ ሐሳብ ስለመኖሩ የተጠየቁት የአንድ ኢትዮጵያዊ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ዘሪሁን ገብረእግዚአብሔር፤ ምክረ ሐሳብ የለም ያሉ ሲሆን፣ "አስቻይ ሁኔታ የለም" የሚል ነው ብለዋል።
ሌላው ምርጫውም ሆነ ሀገራዊ ምክክሩ በተመሳሳይ ወቅት የመጣ በመሆኑ፤ በምክክሩ ወቅት ምርጫ የማያስፈልገው ሁኔታ ከመጣ እንዴት ሊሆን ይችላል የሚል መከራከሪያ ሐሳብ መነሳቱን ገልጸዋል።
ጥቅምት 10 በተከናወነው ውይይት ፓርቲዎች ቦርዱ 7ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ከቀደሙት ተከታታይ ምርጫዎች የተሻለ ዴሞክራሲያዊ፣ አሳታፊ እና ግልጽ እንዲሆን ከወዲሁ የጀመራቸው ተግባራት አበረታች መሆኑን መግለጻቸውን ቦርዱ አንስቷል።

ረቂቅ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳው ታሳቢ ሊያደርጋቸው ይገባል ያሏቸውን ሐሳቦችም አቅርበዋል ብሏል።
ነገር ግን በውይይቱ ተሳታፊ የነበሩት 40 ገደማ ፓርቲዎች በርካቶቹ በጊዜ ሠሌዳው በላይ በምርጫው አስቻይነት ላይ ጠንከር ያለ ውይይት አካሂደዋል።
በውይይቱ ተሳታፊ ከነበሩ ፓርቲዎች መካከል የእናት ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጌትነት ወርቁ በበኩላቸው፤ ውይይቱ ከምርጫ ሠሌዳ ይልቅ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ውይይት እየተካሄደ ያለ የሚመስል እንደነበር ለአሐዱ ተናግረዋል።

አቶ ጌትነት "እንደ እናት ፓርቲም አሁን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ምርጫ ለማድረግ ቀርቶ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ የሚያስችል ሁኔታ የለም" ሲሉ ይሞግታሉ። አስቻይነት ላይ ያተኮረ ውይይት እንጂ 'ምርጫ ይራዘም' የሚል ሐሳብ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
በሀገሪቱ ያሉ ግጭቶች ቆመው፣ ሰላማዊና ታዓማኒ ምርጫ ተካሂዶ ሥልጣን መያዝ የድርጅታቸው ፍላጎት መሆኑን ተናግረዋል።
በውይይቱ ላይ የብልጽግና ፓርቲ ተወካዮችም የተገኙ የነበሩ ቢሆንም፤ በቂ ምላሽ መስጠት አለመቻላቸው በውይይቱ ተሳታፊዎች ተነስቷል።
በተጨማሪም በሰኞ ዕለት ውይይት ከተነሱት መካከል፣ የጸጥታ ክፍሉ ኀላፊዎች ከመከላከያም ሆነ ከፌዴራል ፖሊስ በየዘርፉ ያሉ ኀላፊዎች ተመርጠው ውይይቱ እንዲቀጥል ሐሳብ መነሳቱ ተነስቷል።
አቶ ጌትነት በውይይቱ ወቅት የምርጫ ቦርድ ሰዎች የጊዜ ሠሌዳ ማቅረብ በሕገ-መንግሥቱ የተሰጣቸውን ሥራ ከመሥራት የተለየ አይደለም ሲሉ እንደገለጹላቸው ተናግረዋል።
ነገር ግን፤ ሁላችሁም መንግሥት ላይ ጫና አድርጉ እኛም ውይይቶችን እንቀጥላለን የሚል ሐሳብ መሰንዘሩን ገልጸዋል። ይህንን መረዳታቸውን በሁለተኛው ውይይት ላይ ይዘው ካልመጡ ግን "ወዮ ለራሳቸው" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ሌላው በውይይቱ የተሳተፉት የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ሊቀመንበር መጋቢ ብሉይ አብርሃም ሐይማኖት ናቸው።

የውይይቱ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሠሌዳ ይዞ እንደቀረበ ቢናገሩም፤ በውይይቱ የተንጸባረቀው ሐሳብ ግን የተለየ እንደነበር ገልጸዋል።
ሊቀመንበሩ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ግጭቶች ሳይቆሙ፣ የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞች ሳይፈቱ ምርጫ ማከናወን ለገዢው ፓርቲ ሥልጣንን እንደመስጠት እንደሚቆጠር ይናገራሉ።
ይሁን እንጂ ይህ ምርጫ መበላሸት የለበትም የሚል አቋም እንዳላቸው ገልጸው፤ ቦርዱ ሐላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ማሳሰባቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ምርጫው በውጭ ታዛቢዎች እንዲኖሩ ጥያቄዎች ማቅረባቸውን የገለጹ ሲሆን፤ ቦርዱም ሰላምና ጸጥታን በተመለከተ ከመንግሥት ጋር ውይይት እንዲኖር እንደሚያመቻቹ እንደተገለጸላቸው ነግረውናል።
ሌላው ምርጫውን ለማከናወን እንደ ችግር የተነሳው የሰላምና ጸጥታ ጉዳይ መሆኑን ያነጋገርናቸው ሁሉም ፓርቲዎች ተናግረዋል።
ፓርቲዎቹም እውነተኛ ድርድር በአፋጣኝ ተካሂዶ ሁሉም የሚሳተፍበት ነፃና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲካሄድ ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል።
"ለመሆኑ ይህንን ሁኔታ በቀረው ወራት ውስጥ ማከናወን ይቻላል ወይ?" ስንል የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ሊቀመንበር መጋቢ ብሉይ አብርሃም ሐይማኖትን ጠይቀናል።
በምላሻቸውም መንግሥት ቁርጠኛ መሆን ከቻለ የሰላም ድርድር በአሥራ አምስት ቀንም ሆነ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ማከናወን ይቻላል ሲሉ ተናግረዋል።
መንግሥትም ሆነ ፓርቲዎች ሰላም መሥራት አለባቸው የሚሉት ደግሞ፤ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ሊቀመንበር አብርሃም ጌጡ ናቸው።

ለሰላምና ለሀገር ሉዓላዊነት ክብር እንዲፈታ ከተፈለገ ፓርቲያቸው ከየትኛውም ኃይል ጋር በጋራ ለመሥራት ፍቃደኛ መሆኑን ገልጸዋል። ምርጫ ከማለት አስቀድሞ ሰላም ሊረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
የጊዜ ሠሌዳ መውጣት ጥሩ መሆኑን ያነሱት አቶ አብርሃም፤ ነገር ግን ሀገሪቱ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ መመልከት አለብን ብለዋል። "ነባራዊ ሁኔታ ደግሞ ምርጫ ለማድረግ የሚያስችል ምንም ዓይነት ሁኔታ የለም" ይላሉ።
አቶ አብርሃም ጌጡ ሐሳባቸውን ሲቀጥሉ፤ ቦርዱ አዲስ ባሻሻለው የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጁ ላይ "ፓርቲዎች እጩ አድርገው የሚያቀርቡት አካል ሦስት ሺሕ ሰው ፊርማ ማሰባሰብ አለበት" የሚል ድንጋጌ ማስገባቱን ይናገራሉ።
ይህ ድንጋጌ ማስፈረሙ ሳይሆን ችግር የሆነው፣ ሕጋዊ እውቅና ያለውን አንድ ፓርቲን በአዋጅ ሕገ-ወጥነቱን መጣስ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ይህ አሠራር ከዚህ በተጨማሪ እጩ ቢያስፈርም እንኳን ምን ያህል ሰው ሊመርጠው እንደሚችል መግለጽ ጭምር ነው። በዚህ መሠረት ምርጫው ተከናውኖ "በምርጫው ምንም ድምፅ አላገኛችሁም” ብንባል፣ “የፈረመልን ሦስት ሺሕ ሰው የት ገብቶ ነው?" በሚል የተዓማኒነት ጥያቄ እንደሚያስነሳ ገልጸዋል።
በውይይቱ ወቅት ከፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችና ተወካዮች ለተነሡት ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላተወርቅ፤ ቦርዱ በየአምስት ዓመቱ ምርጫ የማስፈጸም ሕገ-መንግሥታዊ ግዴታ እንዳለበት ገልጸዋል።

በቀጣይም የጸጥታ ሁኔታም ሆነ ተያያዥ ጉዳዮችን ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር ፓርቲዎቹን ያሳተፈ ቀጣይ ውይይት እንደሚኖር አንስተዋል።
ምርጫውን የተመለከቱ ማንኛውም ተግባራት ላይ በቅርበትና በጋራ በመሥራት እንደሚያከናወንም ተናግረዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ