ጥቅምት 13/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በየትኛውም ሁኔታ እያፈራረስነው ያለውን የጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃንን መንግሥት ለማዳን የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን ድጋፍ የሚያደርጉ ጎረቤት ሀገራት ከድርጊታቸው የማይቆጠቡ ከሆነ በድሮን እንደበድባለን ሲል የሱዳን የፈጥኖ ደራሽ ሃይል አስጠንቅቋል፡፡
ለሦስት ቀን ያህል በካርቱም የሚገኘውን የአውሮጵላን ማረፊያ በድሮን እየደበደበ ያለዉ የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ፤ አሁን ደግሞ ለአልቡርሃን መንግሥት ድጋፍ ለማድረግ ሲል በሥም ሳይጠቅስ የከሰሳቸውን ጎረቤት ሀገራት፤ "ከድርጊታቸው የማይቆጠቡ ከሆነ በድሮኖቻችን ኢላማ ይደርጋሉ" ሲል ነው የዛተዉ።
የሱዳን ፈጣኖ ደራሽ ሃይሎች ዋና አዛዣ ጀነራል መሐመድ ሃምዳን ደጋሎ ወይም በቅጥል ስማቸዉ "ሄሜቲ"፤ "ይህ ጠቃሚ መልዕክት ነው" ያሉ ሲሆን፤ "ለረጅም ጊዜ ዝም አል ፤ አሁን ግን ከየትኛውም የጎረቤት ሀገር አየር ማረፊያ የሚነሳ ማንኛውም የአውሮፕላን አቅርቦቶችን አየር ላይ ለማውደም ዝግጁ ነን ብለዋል።
"ይህንን ጥቃት ለመፈፀም እርግጠኛ ነን፤ እናም የማናደርገውን አንናገርም" ሲሉም መናገራቸውን ሚዲል ኢስት ሞኒተርና ሱዳን ትሪቡን ዘግበዋል።
በርግጥ ጀነራል ሄሜቲ በግልፅ ጎረቤት ያሏቸውን ሀገራት በሥም ባይጠቅሱም፤ የሱዳንን ሉዓላዊ መንግሥት በሁለት እግሩ እንዲቆም ቀንደኛ ደጋፊ የሆነችው ሀገር ግብፅ እንደሆነች ይነገራል።
ሄሜቲ የሱዳን የጦር አመራሮች "ሰይጣናዊ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው" ሲሉ ከሰው፤ እናም "ካንሰር" ስለሆኑ መወገድ ያለባቸው ናቸዉ፤ የሱዳንን ሕዝብም በግብዝነት እያታለሉ ነዉ" ብለዋል።
በተጨማሪም "የጦር ሠራዊቱ ዋና አዛዥ ጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን በሠራዊቱ ውስጥ የእስልምና እንቅስቃሴ አራማጅ ናቸው" ሲሉ ሄሜቲ ክሳቸውን ቀጥለው፤ "ወንጀለኛና ነፍሰ ገዳይ" ናቸው ሲሉም ተናግረዋል።
አልቡርሃን ከቀድሞው አገዛዝ መሪዎች ጋር በድብቅ ስለነበራቸው ድብቅ ሴራና ስብሰባ እንደሚያውቁም ገልጸዋል።
ሄሜቲ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉም "የሱዳን ሕዝብ እኝህን ወንጀለኛ አስወግዱ" በማለት፤ "ቀጣይ ድሉ የኛ ነው" ሲሉም ተደምጠዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በመፈራረስ ላይ የሚገኘውን የአልቡርሃን መንግሥትን ለማዳን ድጋፍ የሚሰጡ ሀገራትን ኢላማ እናደርጋለን ሲል የሱዳን የፈጥኖ ደራሽ ሃይል አስጠነቀቀ