ጥቅምት 1/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ዓለም አቀፍ የሴት ሕጻናት ቀን በሲያትል አካዳሚ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት እና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተከብሯል።
በዚህም መድረክ ላይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 10 ኮምፒውተር፣ 240 መፅሐፍት እና 200 የሴቶች ንፅህ መጠበቂያ ኪት ለትምህርት ቤቱ በሽልማት አበርክቷል።
የሲያትል አካዳሚ ምክትል ሥራ አስኪያጅ መምህር ሙሉነህ አያሌው ለአሐዱ እንደገለጹት፤ መስከረም 30 ቀን 2018 ዓ.ም ዓለም አቀፍ የሴት ሕጻናት ቀን በሲያትል አካዳሚ በድምቀት የተከበረ ሲሆን መርሃ ግብሩ በአካዳሚው እንዲከበር የተመረጠበት ምክንያት በቴክኖሎጂ ዘርፉ ላይ በትኩረት ስለሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ምክትል ሥራ አስኪያጁ አክለውም፤ በቴክኖሎጂ ዘርፉ በለተለይም በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ በሌሎች የፈጠራ ውጤቶች ላይ ከታች ከህፃናት ጀምሮ እየሰራ መሆኑን አንስተው፤ በ2017 ዓ.ም ጀኔቫ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ላይ ትምህርት ቤቱን ወክለው የሄዱ ልጆች አምስተኛ ደረጃ ይዘዋል ብለዋል።
በዚህም ሲያትል አካዳሚ ለአርአያነት በመመረጡ ዓለም አቀፍ የሴት ሕጻናት ቀን በአካዳሚው ተከብሮ ውሏል፤ የኮምፒዩተር፣ መፅሐፍት እና ለዓመት የሚሆን ነፃ የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን ተደርጓል በማለት መምህር ሙሉነህ አብራርተዋል።
አካዳሚው ቃሊቲ አካባቢ የሚገኝ ሲሆን፤ በመድረኩም የሴቶች እና ሕጻናት ሚኒስትር ዴኤታ ሂክማ ከይረዲን፣ የአየርላንድ አምባሳደር ኦሊቪያ ሌዝሊ እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት UNFPA የሀገራት ዳሬክተር ኮፊ ኩዋሜ ተገኝተዋል።
በዚህም መርሃ ግብር ላይ ተማሪዎች የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ለታዳሚያን አቅርበዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ