ጥቅምት 1/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት የነበረውና ከኤርትራ ጋር የሚዋሰነው ቃፍታ ብሔራዊ ፓርክ አሁናዊ ሁኔታው በመሻሻሉ፤ ተሰደው የነበሩ 50 ያክል ዝሆኖች ወደ ፓርኩ ተመልሰዋል ሲል የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ለአሐዱ ገልጿል፡፡
"ብሔራዊ ፓርኩ ከሰሜኑ ጦርነት በፊት እንደ ሞዴል የሚወሰድ ነበር" ያሉት የባሰልጣን መስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን መኮንን፤ በ2017 በአማራ ክልል መንግሥት እና በወረዳው በተደረገ ሕግ የማስከበር ሥራ አዎንታዊ ለውጦች ታይተዋል ብለዋል፡፡
በዚህም ከዚህ በፊት ወደ ኤርትራ ተሰደው የነበሩ 50 ዝሆኖች የተመለሱ ሲሆን፤ በውስጡ ያሉ ሌሎች እንስሳትም የመረጋጋት እና ቁጥራቸው የመጨመር ሁኔታ ተስተውሏል ሲሉ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
የሰሜኑን ጦርንት ተከትሎ በፓርኩ ውስጥ ሕገ-ወጥ እርሻ፣ የደን ጭፍጨፋ፣ ሕገ-ወጥ የወርቅ ማዕድን ቁፋሮ፣ እጣን ማውጣት እንዲሁም የመንግሥት አካላት ጭምር የተከዜ ወንዝን በመጠቀም ፓርኩ ውስጥ በመስኖ እርሻ ሲያለሙ እንደነበርም አያይዘው ተናግረዋል፡፡
ሆኖም ከወረዳ እስከ ክልል ድረስ በተሰራው ሕግ የመስከበርና የግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ለውጥ መጥቷል ብለዋል፡፡
ከሕገ-ወጥ የወርቅ ማዕድን ማውጣት እና ከዕጣን ማውጣት ጋር የተያያዙ ሕገ-ወጥ ተግባራት አሁንም ሙሉ ለሙሉ አልተፈቱም፤ በቀጣይም ተጨማሪ ሥራ ይጠይቃል የተባለ ሲሆን አሁን ያለበት ሁኔታ ግን እየተሻሻለ ነው ተብሏል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት ደርሶበት ከነበረው ቃፍታ ብሔራዊ ፓርክ ወደ ኤርትራ የተሰደዱ 50 ዝሆኖች መመለሳቸው ተገለጸ
