መስከረም 19/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ መስከረም 15 ቀን 2018 ዓ.ም ባካሄደው አራተኛ ስብሰባው የብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ተመን (National Bank Rate) አሁን ባለበት 15 በመቶ እንዲቆይ ውሳኔ ማስተላለፉን አስታውቋል፡፡
በዚህም ብሔራዊ ባንክ ለሚሰጣቸው የተቀማጭ ሂሳብ አገልግሎት (standing deposit facility)፣ እና የብድር አገልግሎት (standing lending facility) የሚከፈሉ የወለድ ተመኖች ባሉበት እንዲቀጥሉ፣ እንዲሁም ባንኮች በብሔራዊ ባንክ የሚያስቀምጡት የግዴታ መጠባበቂያ ምጣኔ በነበረበት እንዲቆይ ወስኗል፡፡
እንዲሁም 'በመስከረም ወር ላይ ሊነሣ ይችላል' ተብሎ የተገመተው የባንኮች ዓመታዊ የብድር ዕድገት ጣሪያን ሙሉ ለሙሉ ከማንሣት ይልቅ ገደቡ ለጊዜው ከ18 በመቶ ወደ 24 በመቶ ከፍ እንዲል በስብሰባው ወስኗል፡፡
የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴው ይህንን ጉዳይ በቀጣይ ስብሰባዎቹ ገምግሞ የውሳኔ ሐሳብ እንደሚያቀርብም አስታውቋል፡፡
በተጨማሪም ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ግሽበቱ በሚፈለገው ልክ እንዲሆን ለማስቻል እንደ አስፈላጊነቱ ገበያ-መር የሆኑ የገንዘብ ፖሊሲ መሣሪያዎችን በተናጠልም ሆነ በቅንጅት በቀጣይነት እንደሚጠቀም ገልጿል፡፡
በዚህም እነዚህ የገንዘብ ፖሊሲ መሣሪያዎች የብሔራዊ ባንክ የወለድ ተመን፣ ከባንኮች ጋር የሚደረግ የገንዘብ ግብይት (Open Market Operations)፣ የውጭ ምንዛሪ ገበያ (foreign exchange interventions) እንዲሁም ባንኮች በብሔራዊ ባንክ የሚያስቀምጡት የግዴታ መጠባበቂያ ምጣኔ እንደሚሆኑ አስታውቋል፡፡
ቀጣዩ የኮሚቴው ስብሰባ ታህሳስ ወር 2018 እንዲሆን ተወስኗል፡፡
👉 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ሙሉ መግለጫ ከሥር ተያይዟል



#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ