መስከረም 19/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ካላት የሕዝብ ቁጥር አንጻር 24 የልብ ሕክምና ማዕከላት የሚያስፈልጓት ኢትዮጵያ በሥራ ላይ ያለው ብቸኛው የኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕከል አገልግሎት ከመስጠት አቅም በታች ማለትም በአንድ ሦስተኛው አቅሙ ብቻ እየሠራ መሆኑ ተገልጿል።
ማዕከሉ በየዓመቱ ከ1 ሺሕ 300 በላይ አዳዲስ ታካሚዎችን የሚቀበል ሲሆን፤ ማከም የሚችለው ከፍተኛው ቁጥር እስከ 600 ብቻ መሆኑን የማዕከሉ ኃላፊዎች አስታውቀዋል።
የማዕከሉ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሕሩይ አሊ እንደገለጹት፣ ማዕከሉ 90 ከመቶ በላይ የሚሆነውን የልብ ሕክምና በሀገር ውስጥ መስጠት የሚችል ደረጃ ላይ ቢደርስም፣ በግብዓት እጥረት ምክንያት በአቅሙ ልክ እየሠራ አይደለም።
ይህም በአሁኑ ጊዜ ከ8 ሺሕ በላይ ታካሚዎች ወረፋ እየጠበቁ እንዲቆዩ ማድረጉንና፤ ከዚህም የተነሳ ከተያዘላቸው የሕክምና ቀጠሮ ቀን ሳይደርሱ የሚሞቱ ሕሙማን መኖራቸውን ተናግረዋል።
ሥራ አስፈጻሚው አክለውም፤ "የሕክምና ግብዓት እና የአቅም ችግር ቢፈታ ማዕከሉ በዓመት እስከ 1 ሺሕ 500 ሰው ማከም ይችል ነበር" ብለዋል፡፡
ማዕከሉ 85 ከመቶ የሚሆነውን የሕክምና ግብዓቱን በእርዳታ፣ በድጋፍ እና በግዥ ከውጭ ሀገር እንደሚያገኝ የገለጹም ሲሆን፣ መድኃኒቶቹ በሀገር ውስጥ አለመገኘታቸውና ዋጋቸው ውድ መሆኑ ሌላው ችግር እንደሆነ አስረድተዋል።
ይህን የገንዘብና የግብዓት ችግር ለመፍታት ማዕከሉ እና በተባባሪ አካላት በመተባበር ሕዳር 30 ቀን 2018 ዓ.ም. የሩጫ ውድድር የማካሄድ እቅድ ተይዟል፡፡ 4 ሺሕ ሰዎች እንደሚሳተፉበት በሚጠበቀው በዚህ ውድድር 32 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት ታቅዷል ተብሏል፡፡
''ደጋግ እጆች ለልጆች'' በሚል መሪ ቃል የሚከናወነው ይህ የሩጫ መርሀ-ግብር መስከረም 29/2025 የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የልብ ቀን አስመልክቶ የተዘጋጀ ሲሆን፤ መነሻውም መድረሻውም የልብ ሕሙማን ሕጻናት መርጃ ማዕከል ጊቢ ውስጥ መሆኑም ተገልጿል፡፡

የሩጫ ውድድሩን ከማዕከሉ ጋር በጋራ የሚያካሂደው ጄ ሎርድ ኤቨንት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፋሲካ ገብሬ፤ ይህንኑ ገቢ ለማዕከሉ ለማዋል መታሰቡን በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ አስታውቀዋል።
አቶ ፋሲካ፤ ከሩጫ ውድድሩ የሚገኘው ገቢ ማዕከሉ የአቅሙን ያህል እንዲሠራ ለማገዝ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕከል በአገልግሎቱ 75 ከመቶ የሚሆኑ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትን የሚያስተናግድ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ 25 ከመቶ የሚሆኑት ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ ታካሚዎች ናቸው።
ባለፋት 36 ዓመታ ከ9 ሺሕ በላይ ለሆኑ ሕጻናት የነፃ የልብ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት መስጠቱ የገለጸው ማዕከሉ፤ የልብ ቀዶ ሕክምናን እና በደም ስር የሚሰጥ የልብ ሕክምናን በነጻ እያቀረበ እንደሚገኝ አስታውቋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ