መስከረም 19/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ የደመራ በዓል በተከበረበት መስከረም 17 ቀን 2018 የጉዞ አቅጣጫውን ከሜክሲኮ ወደ ሳር ቤት አድርጎ ሲጓዝ የነበረ ተሽከርካሪ መንገድ ሲያቆርጡ በነበሩ ሁለት ሰዎች ላይ አደጋ በማድረሱ፤ ሕይወታቸው ማለፉን የመዲናዋ ፖሊስ ኮሚሽን ለአሐዱ አስታውቋል።
የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ፤ የሁለቱን ሰዎች ሕይወት ከቀጠፈው የትራፊክ አደጋ በተጨማሪም በተመሳሳይ ዕለት ኮልፌ ቀራኒዮ ወረዳ 10 አካባቢ እቃ የሚያነሳ ፎርክሊፍት ተሸከርካሪ ከሎቤድ ጋር በመጋጨቱ የፎርክሊፍቱ ረዳት ሕይወቱ ማለፉን ለአሐዱ ተናግረዋል።
በዚህም በደመራ በዓል ወቅት በአጠቃላይ የሦስት ሰዎች ሕይወት በትራፊክ አደጋ ማለፉን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ በሁለቱም የበዓል ቀናት የተፈፀመ ወንጀል እንዳሌለ ጠቅሰው፤ በዓሉ በተረጋጋና ሰላማዊ በሆነ መንገድ መከበሩን አስታውቀዋል፡፡
አክለውም በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ለማድረግ ኮሚሽኑ ከባለድርሻ አካላትና ተቋማት ጋር በመቀናጀት ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።
ሕብረተሰቡ ከፖሊስ ጋር የነበረው ትስስር እና መረጃ የመለዋወጥ ሂደት ከፍተኛ እንደነበር የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ በዚህም በበዓሉ ምንም አይነት ወንጀል ሳይፈፀም በሰላም ሊያልፍ ችሏል ብለዋል።
በአዲስ አበባ ከመስቀል አደባባይ ውጭ ከ2 ሺሕ 300 በላይ በሆኑ የተለያዩ ቦታዎች ደመራ መደመሩን እና በሰላማዊ መንገድ መጠናቀቁን የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ማርቆስ ተናግረዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በደመራ ዕለት በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ3 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ
ኮሚሽኑ በመስቀልና በደመራ በዓላት የተፈፀመ ወንጀል አለመኖሩንም አስታውቋል
