መስከረም 13/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮጵያ የባህር በርን በሰላማዊ መንገድ ለማግኘት የሚያስችላት ከጎረቤት ሀገራት ጋር መልካም የሆነ ግንኙነት ሲኖራት እንደሆነ አሐዱ ያነጋገራቸው ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ሳይንስና የዲፕሎማሲ ምሁራን ገልጸዋል።

በሰላማዊ መንገድ መሆኑ ለሁላችንም ትልቅ ጠቀሜታ አለው የሚሉት የዓለም አቀፍ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ደጉ አስረስ (ዶ/ር) የባህር በር የሌለው ሀገር በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ከጎረቤቶቹ የመተላለፊያ መንገድ የማግኘት መብት አለው ብለዋል።

ይህ የሚሆነውም ደግሞ የባህር በር ካለው ሀገር ጋር መስማማት ሲችሉ እንደሆነ ገልጸዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ የባህር በር ማግኘት የምትችለው የዓለም አቀፍ ሕጉን ተፈፃሚ በማድረግና ከጎረቤት ሀገሮች ጋር መልካም ግንኙነት ሲኖር እንደሆነ ተናግረዋል።

ይህ አካሄድ ለሁለቱም ሀገራት ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸው፤ ለአብነትም ኢትዮጵያ የጅቡቲን ወደብ በስፋት እንደምትጠቀምበት አንስተዋል።

ይህም ኢትዮጵያ ወደቧን በመጠቀሟ ብቻ ጅቡቲ ከፍተኛ ገቢ የምታገኝበት እድል መኖሩን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ከዚህ ቀደም ከሱዳን ጋር በነበረው ግንኙነት የሱዳን ወደብ ላይ ለኢትዮጵያ ወደብ የሚሆን ዝግጅት ተጀምሮ እንደነበር አስታውሰዋል።

ከሀገራት ጋር ሰላማዊ ግንኙነት በተጠናከረ ቁጥር ከጎረቤት ሀገራት የሚገኙ ጥቅማጥቅሞች መኖራቸውን የገለጹት ዶ/ር ደጉ፤ በተመሳሳይ ከኤርትራም ጋር እንዲሁ ስምምነት ላይ መድረስ ከተቻለ በሰላማዊ መንገድ ሁለቱም ሀገራት መጠቀም እንደሚችሉ አንስተዋል።

አሐዱ ያነጋገራቸው የቀድሞው ዲፕሎማት ጥሩነህ ዜናው በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት የምትችለው ከጎረቤት ሀገር በመሆኑ በሰላማዊ መንገድ ለማግኘት ለባህር በሩ ባለቤት የሆነው ጎረቤት ሀገር መስማማት ሲችል እንደሆነ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር በሰላማዊ መንገድ የባህር በር እንዲኖራት እንደምትፈልግ በተደጋጋሚ ጊዜ መግለጿን ያነሱት የቀድሞው ዲፕሎማት፤ ይህንን እውን ለማድረግ የሁለቱም ሀገራት መልካም ስምምነት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በመሆኑም በሰላማዊ መንገድ የባህር በር ለማግኘት ያለው አማራጭ ከጎረቤት ሀገራት ጋር መልካም ግንኙነትን በመፍጠር ሊሆን እንደሚገባ የገለጹ ሲሆን፤ ለዚህም የመስጠትና መቀበል አሰራር ሲኖር እንደሆነ ጠቁመዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ