መስከረም 13/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የቃል ኪዳን ቤተሰብ ዓላማን ለማህበረሰቡ የማስገንዘብ ሚና ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ይጠበቃል ሲል የጎንደር ዩኒቨርስቲ አሳስቧል።

ዩኒቨርስቲው ላለፉት ስድስት ዓመታት ከሦስት ሺሕ በላይ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች በጎንደር የቃል ኪዳን ቤተሰብ ውስጥ እንደታቀፉ ገልጿል፡፡

የጎንደር ቃልኪዳን ቤተሰብ ማስተባባሪያ ፅሕፈት ቤት ኃላፊ ታደሰ ወልደገብርኤል (ዶ/ር) ለአሐዱ እንደተናገሩት፤ የጎንደር ቃል ኪዳን ቤተሰብ በስድስት ዓመት ውስጥ ውጤታማ መሆን ችሏል፡፡

የቃል ኪዳን ቤተሰብን በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንውን እንዲሆን ለማስቻል፤ ማህበረሰቡን ስለቃል ኪዳን ቤተሰብ የማሳመን እና አላማውን የማስረዳት ከፍተኛ ጥረት እንደሚጠይቅ ገልጸዋል፡፡

ከ2012 ዓም ጀምሮ ለ3 ሺሕ 500 የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች በጎንደር ቃልኪዳን ቤተሰብ ታቃፊ ሲሆኑ፤ ከ6 ሺት በላይ የሚሆኑ ወላጆች አባል እንደነበሩም ኃላፊው አስታውሰዋል።

የጎንደር ቃልኪዳን ቤተሰብ ማስተባባሪያ ፅፈት ቤት በተጀመረ በአንደኛው ዓመት ከ1 ሺሕ 500 በላይ ተማሪዎች በቃል ኪዳን ቤተሰብ ውስጥ መታቀፋቸውን አውስተዋል፡፡

እንዲሁም በ2018 የትምህርት ዘመን ወደ አንድ ሺሕ የሚጠጉ ወላጆች በጎንደር የቃልኪዳን ቤተሰብ አባል ለመሆኑ በወላጆች ባንክ እንደተመዘገቡ ተናግረዋል፡፡

ተማሪዎቹ በቃል ኪዳን ቤተሰብ ወላጅ የሚያገኙት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በኃላፊነት በሚያገለግሉ እንዲሁም በማህበረሰቡ ውስጥ ባሉ በጎ ፈቃደኞች እንደሆነ የገለጹም ሲሆን፤ የቃል ኪዳን ቤተሰብ ውስጥ አባል ለመሆን በትዳር ዓለም ላይ የሚገኙ እንዲሁም በሥራ ላይ ያሉ ሊሆኑ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በዚህም መሠረት ኮሚቴ በማቋቋም ተማሪዎች ለቃል ኪዳን ቤተሰብ እንዲመረጡ ይደረጋል ያሉት ኃላፊው፤ መስፈርቱን ግን ማሟላት ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህም የቃል ኪዳን ቤተሰብ የከፍተኛ ትምህርታቸውን ለመከታተል ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ወደ ጎንደር ዩኒቨርሲቱ ለሚያቀኑ ተማሪዎች ከቀለም ትምህርት በተጨማሪ የጎንደርን አኗኗርና ዘይቤን እንዲያውቁ አስቻይ ሁኔታን ለመፍጠር ያለመ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎቹ በትምህርት ቆይታቸው የቤተሰብነት ስሜት እንዲሰማቸው እና አብሮነትን ለማጠናከር እንዲቻል የታለመ እንደሆነም አክለው ገልጸዋል፡፡

በ2012 ዓ.ም የጎንደር ቃል ኪዳን ቤተሰብ በፕሮጀክት ደረጃ የተመሰረተ እንደነበር የሚያስታውሱት የጽህፈት ቤቱ ኃላፊው፤ በ2016 ዓም ወደ የጎንደር ቃል ኪዳን ቤተሰብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ሊያድግ ችሏል ብለዋል፡፡

በዚህ ረገድ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የመጀሪያውን የጎንደር ቃል ኪዳን ቤተሰብ የልምድ ልውውጥ በሐምሌ ወር 2017 መከናወኑን አስታውሰዋል፡፡

በ2018 ዓ.ም በአዳማ ዩኒቨርሲቲ የቃል ኪዳን ቤተሰብ ማስጀመርያ መርሃ ግብር መከናወኑን በማስታወስም፤ ሌሎችም የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ወደ ትግበራ ለመግባት በሂደት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ