መስከረም 14/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ የቡና እና ሻይ ባለስልጣን ከ30 ዓመታት በፊት ዝቅተኛ ምርት ይሰጡ የነበሩ የቡና ዝርያዎችን በማዘመን፤ የሀገሪቱን የቡና ምርት በ4 እጥፍ ማሳደግ መቻሉን አስታውቋል።

ለዚህ ስኬት ዋነኛው ምክንያት በሽታን የመቋቋም አቅም ያላቸው እና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የሚስማሙ የቡና ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ በማድረጉ መሆኑን ያስታወሰው ባለስልጣኑ፤ ዝርያቸው የተሻሻለ ምርቶችን ለአርሶ አደሩ ማቅረብ እንደሚገባ ገልጿል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ለአሐዱ እንደተናገሩት፤ ከ5 ዓመታት በፊት ከ500 ሺሕ ቶን የነበረውን የቡና ምርት በከፍተኛ ሥራ ወደ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ቶን ማሳደግ ተችሏል።

ይህ የቡና ምርት ዕድገት ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።

Post image

ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም፤ "ምርትን ማሳደግ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ አያደርግም። የዓለም አቀፍ የቡና ዋጋ ተለዋዋጭ በመሆኑ፣ ይህንን መቋቋም የሚችል የቡና አይነት ለገበያ ማቅረብ ወሳኝ ነው" ብለዋል።

በዚሁ መሠረት፣ ባለስልጣኑ ቀደም ሲል በኒውዮርክ ገበያ በጨረታ ይሸጥ የነበረውን የኢትዮጵያ ቡና፤ አሁን ባለው የግብይት ስርዓት ውድድር ባለው ገበያ ላይ እንዲቀርብ በማድረግ ለውጥ ማምጣቱን አስታውቀዋል።

በተጨማሪም፤ ሕገ-ወጥ የቡና ንግድን በመቀነስ የውጭ ምንዛሪ ገቢን ማሳደግ እንደተቻለ ገልጸዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ