መስከረም 14/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በደቡባዊ ቻይና እና ታይዋን በተከሰተውና 'ራጋሳ' በተሰኘው ከባድ አውሎ ነፋስ ምክንያት፤ በታይዋን እስካሁን ቢያንስ የ14 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተገልጿል፡፡

ትናንት ማክሰኞ በታይዋን ሁዋሊየን ከተማ በደረሰው ከባድ ዝናብ የቀላቀለ አውሎ ነፋስ ምክንያት በግዛቱ የሚገኝ ትልቅ ግድብ የፈረሰ ሲሆን፤ ይህንንም ተከትሎ በድንገት የተለቀቀው ከፍተኛ የውሃ ፍሰት ምክንያት በአቅራቢያው በሚገኙ አካባቢዎች በጎርፍ መጥለቅለቅ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

ከባድ አውሎ ነፋሱ በሆንግ ኮንግ በርካታ ዛፎችን ጥሏል፣ በጎርፍ መጥለቅለቁ ምክንያትም በብዙ መንደሮች ውስጥ የሚገኙ በርካታ ቤቶች ወድመዋል ንብረቶችም በጎርፍ ተወስደዋል፡፡

Post image

አሁን ላይ 'ራጋሳ' የተሰኘው ይህ አውሎ ንፋስ ከሆንግ ኮንግ ቀስ በቀስ እየራቀ መሆኑ የተገለጸ ቢሆንም፤ "ከተማዋ አሁንም በአውሎ ንፋስ ትመታለች" ሲል የሆንግ ኮንግ ኦብዘርቫቶሪ ትናንት ምሽት በሰጠው የማስጠንቀቂያ መልዕክት አስታውቋል።

"ራጋሳ 'ከፍተኛ ማዕበልን' አምጥቷል፣ በባህር ዳርቻዎች ላይ ያሉ ውሃዎች ከነበራቸው ደረጃ ከ3 ሜትር በላይ ከፍ ብሏል" ሲልም አስታውቋል።

በተመሳሳይ ከፍተኛ የጎርፍ መጥለቅለቅ ባጋጠመው ማካው ከተማም፤ በአንዳንድ ዝቅተኛ ቦታዎች ላይ የኃይል አቅርቦት መቋረጡ ተገልጿል፡፡

በታይዋን በአውሎ ንፋሱ ግፊት ምክንያት አስርት ዓመታትን ያስቆጠረው ግድብ መደርመሱን ተከትሎ፤ ቢያንስ 14 ሰዎች ሲሞቱ 18 መቁሰላቸው ነው የተነገረው። በተጨማሪም 124 ያህል ሰዎች የደረሱበት አልታወቀም ተብሏል፡፡

Post image

አውሎ ንፋሱ ሰሜናዊ ፊሊፒንስን አቋርጦ በነበረበት ወቅትም፤ ቢያንስ የሁለት ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተገልጿል።

በተመሳሳይ በቻይ ዋን ግዛት "አንድ የአምስት ዓመት ልጅ እና እናቱ ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ ያለውን ማዕበል እየተመለከቱ ባለበት ወቅት ወደ ባህር ውስጥ ወድቀዋል" ሲል የግዛቷ ፖሊስ የገለጸ ሲሆን፤ ሁለቱም ወደ ሆስፒታል ቢወሰዱም አሁን ላይ ለሕይወት በአስጊ በሆነ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ አመላክቷል፡፡

ቤተሰቦቹን ለማዳን ወደ ውሃው ውስጥ ዘልለው የገቡት የልጁ አባትም፤ በሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ፖሊስ ማስታወቁን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡

Post image

የቻይና የአደጋ ጊዜ አስተዳደር ሚኒስቴር፤ "አውሎ ነፋሱ ከእኩለ ቀን ጀምሮ እስከ ዕረቡ መጨረሻ ድረስ በጓንግዶንግ የባህር ዳርቻ በዙሃይ እና ዣንጂያንግ ከተሞች ይከሰታል" ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቋል።

በሜይን ላንድ ቻይና ያሉ ባለስልጣናት በደቡብ የሀገሪቱ ክፍል ቢያንስ በ10 ከተሞች የሚገኙ የንግድ ሱቆች እና ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ትዕዛዝ ያስተላለፉ ሲሆን፤ ይህም በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚመለከት መሆኑ ተነግሯል።

በተለምዶ በእንቅስቃሴ የተጨናነቀው የያንግጂያንግ ባቡር ጣቢያም አገልግሎቱን ያቆመ ሲሆን፤ በዛሬው ዕለትም በጓንግዶንግ ግዛት የባቡር ጉዞ ታግዷል።

ባለስልጣናት እንዳሉት ከ885 በላይ ሰዎች በሆንግ ኮንግ በሚገኙት 50 ጊዜያዊ መጠለያዎች ተጠልለዋል።

በቻይና ደቡብ ምስራቅ ሼንዘን 400 ሺሕ ሰዎች አካባቢያቸውን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ የተላለፈ ሲሆን፤ በደቡባዊው የጓንግዶንግ ግዛት ውስጥም ቻኦዙ፣ ዙሃይ ፣ ዶንግጓን እና ፎሻን ከተሞች ላይ የተለያዩ የአደጋ መከላከል እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው ተብሏል።

Post image

በዚህም ከባድ አውሎንፋስ ምክንያት በደቡባዊ ቻይና ጓንግዶንግ ግዛት ብቻ ከ2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መፈናቀላቸው ተነግሯል፡፡

የቻይና የአደጋ ጊዜ ሚኒስቴርም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ድንኳኖች፣ ታጣፊ አልጋዎች፣ የመብራት መሳሪያዎች እና ሌሎች የነፍስ አድን አቅርቦቶችን አደጋ ወደደረሰባቸው አካባቢዎች ልኳል ሲል የቻይና መንግሥት ሚዲያ ዘግቧል።

የሳይንስ ምሁራን የአየር ንብረት ለውጥ በሚያስከትለው ተጽእኖ ምክንያ የዓለም ሙቀት እየጨመረ በመምጣቱ ፤አውሎ ነፋሶች የበለጠ ኃይለኛ እየሆኑ መጥተዋል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ