መስከረም 14/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በመጪዎቹ ጊዜያት በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚጠበቀው ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ ለከፍተኛ እና ድንገተኛ የጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ያደርጋል ሲል የኢትዮጵያ ሜቲዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስጠንቅቋል።

ኢንስቲትዩቱ በትንበያው በተለይም በአዋሽ፣ በስምጥ ሸለቆ፣ በኦሞ-ጊቤ እና በዋቢ ሸበሌ ተፋሰሶች ላይ መጠነኛ እና ከፍተኛ የጎርፍ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል አመላክቷል።

በኢንስቲትዩቱ የትንበያ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አሳምነው ተሾመ (ዶ/ር)፤ "በተያዘው ዓመት ከአምናው የክረምት ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከመደበኛ በላይ የሆነ የዝናብ መጠንና ስርጭት ታይቷል" ሲሉ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

በ24 ሰዓት ውስጥ በሰዓት ከ30 እስከ 185 ሚሊ ሜትር የሚደርስ ከፍተኛ የዝናብ መጠን በ464 የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ መመዝገቡ፣ በአሁን ሰዓት ያለው የውሃ መጠን ከወትሮው በእጅጉ ከፍ ያለ መሆኑን እንደሚያመለክት ያብራሩት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ክስተቱ በ12 ዋና ዋና ተፋሰሶች ላይ ያለው ውሃ የመያዝ አቅም በመጨመር የጎርፍ አደጋን የመፍጠር አቅሙን ከፍ ያደርጋል ብለዋል።

ትንበያ መረጃዎቹ እንደሚያሳዩት በቀጣዮቹ 10 ቀናት በአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ የዝናብ መጠን እንደሚጠበቅና ይህም እስከ ጥቅምት ወር መጀመሪያ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ኢንስቲትዩቱ ይህን አደጋ ለመከላከል ቦታ ተኮር የሆኑ ትንበያዎችንና የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎችን በየቀኑ፣ በየአስር ቀኑና በየወሩ በማዘጋጀት ለባለድርሻ አካላት እያቀረበ እንደሚገኝ ገልጿል።

በተጨማሪም፣ ኢንስቲትዩቱ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሜትሮሎጂ ጣቢያዎችን በማቋቋም መረጃዎችን በመሰብሰብና በማደራጀት የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ትንበያዎችን በመስጠትና የቅድመ ማስጠንቀቂያ መልዕክቶችን በማስተላለፍ ላይ መሆኑን አስታውቋል።

"ይህ ሁሉ ጥረት የሚደረገው የአየር ሁኔታ ለውጦች በግብርና፣ በውሃና በአካባቢ ላይ ሊያስከትሉት የሚችሉትን አደጋ ለመቀነስ ነው" ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ በመሆኑም ነዋሪዎችና የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ይህን አስደንጋጭ መረጃ በከፍተኛ ጥንቃቄ ሊመለከቱትና አስቀድመው ለመከላከል የሚያስችሉ እርምጃዎችን ሊወስዱ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተውበታል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ