ጥቅምት 12/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ወደ 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚጠጋ የግሪሳ ወፍ መንጋ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የክልሉ ግብርና ቢሮ ለአሐዱ አስታውቋል።
ይህ ከፍተኛ መጠን ያለው አጥፊ የወፍ መንጋ በክልሉ በሚገኙ የእርሻ ሰብሎች ላይ አነስተኛ ጉዳት እንዳስከተለ እና በተለይም በምሥራቅ ሐረርጌ፣ በማዕከላዊና ምሥራቅ ሸዋ ዞኖች ላይ ተከስቶ እንደነበር ተገልጿል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የሰብል ጥበቃ ኃላፊ አቶ ደጀኔ ኢብሳ እንዳሉት፤ ከጠቅላላው የወፍ መንጋ መጠን 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን የሚሆነውን የግሪሳ ወፍ ማጥፋት ተችሏል።
ኃላፊው አክለውም፤ "የወፍ መንጋውን ለመከላከል በአውሮፕላን የመድኃኒት ርጭትን ጨምሮ ሌሎች መንገዶች ጥቅም ላይ ውለዋል" ብለዋል፡፡
በክልሉ ከግሪሳ ወፍ መንጋ በተጨማሪ ከ146 ሺሕ ሔክታር በላይ ሰብል ላይ የተከሰተውን "የስንዴ ዋግ" በሽታ በመድኃኒት መቆጣጠር እንደተቻለ ገልጸዋል።
በሩዝ፣ በበቆሎ፣ በባቄላ እና መሰል የሰብል አይነቶች ላይ የሚያጋጥመውን የበሽታዎቹን ስርጭት ለመግታትና ጉዳቱን ለመቀነስ የመከላከል ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል።
በ2018 ዓ.ም. የመኸር ወቅት አጠቃላይ በክልሉ 8 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሔክታር የእርሻ መሬት በሰብል እንደተሸፈነ የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ ያመለክታል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ