ሕዳር 22/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በትራፊክ አደጋ ጉዳት ደርሶበት ወደ ሕክምና ተቋማት ያመራ ማንኛውም ሰው እስከ 15 ሺሕ ብር የሚደርስ አስቸኳይ የነፃ ሕክምና አገልግሎት እንዲያገኝ የሚፈቅደውን መመሪያ ተግባራዊ የማያደርጉ ተቋማት እና ባለሙያዎች በሕግ ይጠየቃሉ ተብሏል።
የመንገድ ደህንነት እና መድኅን ፈንድ አገልግሎት እንዳስታወቀው፤ የመንግሥትም ሆነ የግል የሕክምና ተቋማት ጉዳት ደርሶበት የሚመጣን ማንኛውም ግለሰብ በነፃ የመርዳት ግዴታ ቢኖርባቸውም አንዳንድ ተቋማት በመመሪያው የታዘዘውን አሰራር ተግባራዊ እያደረጉ አይደለም፡፡

"መመሪያውን ተላልፈው የተገኙ የሕክምና ባለሙያዎች እና ተቋማቱ እርምጃ ይወሰድባቸዋል" ሲሉ ማስጠንቀቂያ የሰጡት የአገልግሎቱ የሕዝብ ግንኙነት አስተባባሪ አቶ ሱራፌል ብርሃኑ፤ ሁሉም የሕክምና ተቋማት ለትራፊክ አደጋ ተጎጂዎች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ አስቸኳይ የሕክምና እርዳታ መስጠት እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተውበታል።
ይህ ግዴታ የተቀመጠው ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሆነ ያስታወሱት አስተባባሪው፤ በወቅቱ የወጣው ተቋማቱ እስከ 2 ሺሕ ብር የሚደርስ ሕክምና በነጻ እንዲሰጡ የሚያዘው መመሪያ ተሻሽሎ ወደ 15 ሺሕ ብር መሻሻሉን ለአሐዱ ሬዲዮ ተናግረዋል።
አስተባባሪው አቶ ሱራፌል፤ "ምንም እንኳን ሥልጠና እና መመሪያ በተደጋጋሚ ቢሰጥም፣ ጥቂት የማይባሉ የጤና ተቋማት 'ሕጉን አላውቀውም' የሚል ምክንያት አገልግሎቱን ከመስጠት መቆጠባቸው ለቅጣት ይዳርጋቸዋል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ተመሳሳይ ጥፋት የተገኘባቸው ሕግን የማያከብሩ ተቋማትን በወጡ ደንብና መመሪያዎች መሠረት ተጠያቂ ለማድረግም ለሕግ አስከባሪ አካላት ሥልጠና እንደሚሰጥ አብራርተዋል።
የጤና ተቋማት ለነፃ አስቸኳይ ሕክምና ያወጡት ወጪ ተመላሽ እንደሚደረግ ያስረዱት አቶ ሱራፌል፤ ፈንዱ ይህንን ነፃ አስቸኳይ ሕክምና ለማስፈጸም የሚያስችል ገንዘብ የሚያሰባስበው ከራሱ መዋጮ በተጨማሪ ከኢንሹራንስ ኩባንያዎች እንደሆነ ተገልጿል።
የተሰበሰበው ገንዘብ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ለተጎጂዎች ድጋፍ ይውላል ተብሏል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ