ሐምሌ 3/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ አለመግባባቶች ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ሰብአዊ ኪሳራ እያስከተሉ እንደሚገኙ ያነሱት አሐዱ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) እና የእናት ፓርቲ ተወካዮች "ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ ግጭት ቀስቃሽ ምልክቶች ሲታዩ በፍጥነት ለማጥፋት መጣር ይገባል" ብለዋል።
ግጭቶችን 'መግታት ወይም ማስታገስ የሚጠይቁ' እና 'መፍትሔ የሚጠይቁ' በሚል በ2 ከፍለው የተመለከቱት የኢሕአፓ የአዲስ አበባ ኮሚቴ አስተባባሪ አበበ አካሉ ናቸው።
ማስታገስ የሚለው አማራጭ የግጭቶቹ ምልክቶች ላይ ለመሥራት የሚያግዝና ጊዜያዊ መፍትሔ እንደሆነ ያብራሩት አቶ አበበ፤ "ግጭቱ ከመፈንዳቱ በፊት የሚታዩ ምልክቶችን የከፋ ነገር ከማስከተላቸው በፊት በማስታገስ አስከፊ ውድመትን ማስቀረት ያስችላል" ብለዋል።
"የችግሩን መሠረታዊ ጉዳይ በመለየት መፍትሔ መስጠት ዋነኛው አማራጭ ነው" ያሉት ፖለቲከኛው፤ "ይህኛውን አማራጭ ለመከተል መሠረታዊውን ጉዳይ መለየት ያስፈልጋል። የኃይል አማራጭ ዘላቂ መፍትሔ አያመጣም" በማለት አብራርተዋል።
የእናት ፓርቲ አባል አቶ ጌትነት ወርቁ በበኩላቸው፤ "የችግሩን ምንጭ ማወቅ ብቻ ሳይሆን ለተግባራዊነቱ ቁርጠኛ መሆን ያስፈልጋል" ብለዋል።
"ሁሉም የግጭት መነሻ የሆኑ ችግሮች በሕጋዊ መንገድ ብቻ አይፈቱም። አንዳንዶቹ ፖለቲካዊ መፍትሔ ያስፈልጋቸዋል" ያሉት ፖለቲከኛው፤ "ጦርነት ችግርን ያባብስ እንደሆነ እንጂ፤ መፍትሔ አይሰጥም" ሲሉም ተናግረዋል።
"ግጭት የሂደቱ መጨረሻ ነው ግጭቱ ከመፈንዳቱ በፊት አመላካቾች አሉ" የሚሉት አቶ ጌትነት፤ "ምልክቶችን ማጥፋት ላይ ቀድሞ ተሠርቶ ቢሆን አሁን ወደ አለው ችግር ባልተገባ ነበር" ብለዋል።
አክለውም፤ ጥያቄዎች ለመንግሥት የሚቀርቡት አስተማማኝ ሰላም ሲኖር፣ የመኖር ዋስትና ሲረጋገጥ እንደሆነ አስረድተዋል።
ከመንግሥት የሚጠበቀው ተቀዳሚ ተግባር ለልማት ምቹ የሆነ ሰላማዊ ከባቢ መፍጠር ነው፤ ዜጎች በሰላም ወጥተው በሰላም የሚገቡበትን ሁኔታ ማረጋገጥ ከመንግሥት ይጠበቃል ሲሉም የፓርቲዎቹ ተወካዮች አሳስበዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
የቅራኔ ምልክቶችን በፍጥነት በማጥፋት አለመግባባትን ማስቀረት እንደሚቻል ፓርቲዎች ገለጹ
