ሐምሌ 2/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ በሚገኘው የሕጻናት ማረሚያ ማዕከል ውስጥ በወንጀል ነክ ጉዳዮች ላይ የተጠረጠሩ 117 የሚሆኑ ሕጻናት እንደሚገኙ የአዲስ አበባ ሴቶች፣ ሕጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ለአሐዱ አስታውቋል።

የቢሮው የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሀድጉ ፀሀዬ ለአሐዱ እንደተናገሩት፤ ቢሮው ሕጻናትን በተመለከተ በተለያዩ ዘርፎች በማዋቀር የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል፡፡

ከሚሰራቸው ሥራዎች መካከልም የተጣሉና ወላጆቻቸው ሊገኙ ያልቻሉ ሕጻናትን የማቆያ ቦታ በማዘጋጀት እንደሚያኖር ተናግረዋል። በተጨማሪም ወደ ሲቪል ማህበራት ጋር በማገናኘት ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግ አንስተው፤ የጉዲፈቻ አገልግሎት እንደሚሰጥም አስታውቀዋል።

ከዚህ ሌላ ግን በተለያዩ ምክንያቶች ሕጻናት ለወንጀል በሚጋለጡበት ወይም ደግሞ በሚጠረጠሩበት ጊዜ ቀጥታ ወደ ቢሮው እንደሚገቡ እና ከዛ በኋላ ባለው ሂደትም ወደ ህፃናት ማረሚያ ማዕከል እንዲገቡ የማድረጉን ሥራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ውሳኔ እየተሰጠባቸው የሚወጡና አዳዲስ የሚገቡ ስለሚኖሩ ቁጥሩ ቋሚ እንደማይሆን ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ በአሁኑ ወቅት 117 የሚደርሱ ታዳጊ ሕጻናት በማዕከሉ የተሀድሶ ስልጠና እየተሰጣቸው እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ሕጻናቱ በተጠረጠሩበት ወንጀል ልደታ እና ቦሌ የፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት በሚገኘው ተስማሚ የሕጻናት ችሎት ውሳኔ እንደሚሰጣቸውም አንስተዋል።

በሕጻናት ማረሚያ ማዕከሉ ውስጥ እድሜያቸው ከ9 እስከ 14 ዓመት የሆኑት እንደሚገቡ ገልጸው፤ "17 ዓመት ሲሞላቸው ግን ውሳኔ የተወሰነባቸው ከሆነም ከማዕከሉ እንዲወጡ በማድረግ በፍትህ ሚኒስቴር በኩል ወደ መደበኛ የፍርድ ቦታ እንዲሄዱ ይደረጋል" ብለዋል።

በማዕከሉ የሚገቡት በአብዛኛው ሕጻናት ውጤታማ ሆነው እንደሚወጡ የገለፁት ዳይሬክተሩ፤ ትምህርትን ጨምሮ የተለያዩ የሙያ እና የሳይኮሎጂ ስልጠናዎች እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ