መስከረም 13/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በትግራይ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ድምጽ ሊሆኑ ይገባል ሲሉ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠይቀዋል፡፡
በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰውና በፕሪቶሪያ ስምምነት የተቋጨው ጦርነት በርካታ ዜጎችን ከቤት ንብረታቸው ማፈናቀሉ ይታወሳል።
በዚህም በጦርነቱ ወቅት ከቀያቸው የተፈናቀሉ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች በትግራይ በተለያዩ አካባቢዎች በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡
የፕሪቶሪያው ስምምነት ውስጥ ተፈናቃዮችን የመመለስ ሥራ ቢካተትበትም ተግባራዊ ሳይደረግ በመቆየቱ ተፈናቃዮች ችግር ውስጥ ናቸው የሚሉት፤ የሳልሳይ ወያነ ትግራይ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ብርሃነ አፅብሃ ናቸው።
በፌደራል መንግሥት በኩል ተፈናቃዮችን እንመልሳለን' የሚሉ መግለጫዎች ቢሰጡም፤ "ህወሓት በምርጫ ቦርድ መሰረዙን ተከትሎ 'ተፈናቃዮች ህወሓት ወደቀደመ ሕጋዊ ሰውነቱ ሳይመለስ አልመለስም' ብለዋል" የሚል ፓለቲካዊ አካሄድን እየተከተለ ነው ብለዋል።
ተፈናቃዮች ሲመለሱ ዋስትናቸው ተጠብቆ መሠረታዊ ነገሮች ተሟልተውላቸው መሆን እንዳለበትም ጠቁመዋል።
የአረና ትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አምዶም ገብረስላሴ በበኩላቸው፤ ተፈናቃዮች ያሉበት የመጠለያ ጣቢያዎች ምቹ አለመሆናቸው የገለጹ ሲሆን፤ ተፈናቃዮች ለበርካታ ችግሮች እየተዳረጉ ነው ብለዋል።
"ተፈናቃዮች ወደመኖሪያቸው የመመለስ ፍላጎት ቢኖራቸውም ህወሓት ከራሱ ህልውና ጋር ያያዘው በመሆኑ መመለስ አልቻሉም" ሲሉ የቀደመውን ሀሳብ የተጋሩ ሲሆን፤ የፌደራል መንግሥት ኃላፊነቱን እየተወጣ አለመሆኑን ጠቅሰዋል።
በተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ መሆናቸውን እንዲሁም ነዋሪዎቹ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብታቸው እየተከበረ ባለመሆኑ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድምጽ ሊሆናቸው እንደሚገባ ነው የገለጹት።
እንዲሁም ሁለቱን አካላት በማደራደር ሂደት ውስጥ የነበሩ ሀገራት ኃላፊነታቸው እንዲወጡ ተጠይቋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በትግራይ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ድምጽ ሊሆን እንደሚገባ ተገለጸ
