ሐምሌ 1/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በትናንትናው ዕለት ሰኔ 30 ቀን 2017 የቀድሞው የሰላም ሚኒስቴር ዲኤታ አቶ ታዬ ደንደአ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የሽብር እና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ችሎት የቀረቡ ሲሆን ሦስት የመከላከያ ምስክሮቻቸው ግን አሁንም በችሎት አልተገኙም ተብሏል፡፡
አቶ ታዬ ሁከትና ብጥብጥ በማነሳሳት፣ ፀረ-ሰላም ኃይሎችን በመደገፍ እንዲሁም የጦር መሳሪያ ሕጉን በመተላለፍ ተደራራቢ ወንጀሎች ተከሰው በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኝ ይታወቃል።
በመሆኑም በትናንትናው ዕለት የጦር መሳሪያ ሕጉን በመተላለፍ በተጠረጠሩበት የወንጀል አይነት ቀሪ ሦስት የተከላካይ ምስክሮች እንዲቀርቡ ተቀጥሮ የነበረ ሲሆን፤ ምስክሮቹ በችሎት እንዳልቀረቡ አሐዱ በቦታው ተገኝቶ አረጋግጧል።
ተከሳሽ ከዚህ በፊት 5 የተከላካይ ምስክሮች ያቀረቡ መሆኑ ይታወሳል።
በዚህም ሕዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ሁለቱ ማለትም፤ የፖሊስ ኮሚሽነር መላኩ ፈንታና አምባሳደር ብናልፍ አንዷለም ለፍርድ ቤቱ በፅሁፍ የምስክርነት ቃላቸውን የሰጡ መሆኑን መዘገባችን የሚታወስ ነው።
ይሁን እንጂ ቀሪዎቹ ሦስት የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የመከላከያ ምስክሮች ትናንትም ለ3ተኛ ጊዜ የመከላከያ ምስክርነታቸውን ለመስጠት በችሎቱ አለመገኘታቸውን አሐዱ በቦታው ተገኝቶ ተመልክቷል፡፡
እንዲሁም በዋስትና ተሰጥቶባቸው የነበሩ እና ዐቃቤ ሕግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ በማለት ውድቅ የተደረጉ ክሶችን በተመለከተ በሁለቱ ክሶች ማለትም ሁከትና ብጥብጥ በማነሳሳት፣ ፀረ-ሰላም ኃይሎችን በመደገፍ በሚሉ ክሶች ደግሞ በትናንትናው ዕለት ሁለት የመከላከያ ምስክሮች ቃላቸውን የሰጡ መሆኑ ተገልጿል።
ስለሆነም ፍርድ ቤቱ ግራ ቀኙን መስቀለኛ ጥያቄ እንዲሳ ካደረገ በኋላ መዝገቡን ተጨማሪ የመከላከያ ምስክር እንዲቀርብ ለሐምሌ 11/2017 ዓ ም ተቀጥሯል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
የቀድሞው የሰላም ሚኒስቴር ዲኤታ አቶ ታዬ ደንደአ ሦስት የመከላከያ ምስክሮች በችሎት አለመቅረባቸው ተገለጸ
