ሐምሌ 1/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን በዳሰነች ወረዳ የኦሞ ወንዝ መሙላቱን ተከትሎ ከ65 ሺሕ በላይ ዜጎች ከቀዬአቸው መፈናቀላቸው ተገልጿል፡፡
በዚህም ከ15 ሚሊዮን በላይ የዋጋ ግምት ያላቸው የሰብአዊ እርዳታዎችን ለተፈናቀሉ ዜጎች ማቅረብ መቻሉን በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ለአሐዱ አስታውቋል።
የኦሞ ወንዝ በከፍተኛ ሁኔታ በመሙላቱ በርካታ አርብቶ አደሮችን ከቀዬያቸው ማፈናቀሉን ለአሐዱ የገለጹት፤ የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ተስፋዬ ዱንዳ ናቸው።
ተፈናቃዮች በጊዜያዊ ማቆያ ስፍራ እንዲቆዩ መደረጉን የገለጹት ኃላፊው፤ የምግብ እህልና መጠጦች፣ የሕክምና መገልገያዎች እና ሌሎች ግብዓቶች እንደቀረቡላቸው አስታውቀዋል።

በአሁኑ ወቅት የውሃው መጠን ከተለመደው ውጪ እየጨመረና ሰፊ ቦታ እየያዘ ከመምጣቱ የተነሳ ለኦሞራቴ ከተማ ማህበረሰብም አደጋው እንደሚያሰጋ ተናግረዋል።
ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ በመቀናጀት ውሃው ወደ ከተማውና መንደሮች ዘልቆ እንዳይገባ የግድብ ሥራ በመስራት ጊዜያዊ መፍትሄ የመስጠት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የውሃውን አቅጣጫ የማስቀየርና የማፋሰስ ሥራዎች ከዚህ ቀደም የተጀመሩ ቢሆንም፤ በባለሃብቶች እርሻ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያስከተለ በመሆኑ በጅምር መቆሙን አስታውሰዋል። በቀጣይ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተማከሩ መሆኑንም ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡
አያይዘውም፤ በተደጋጋሚ የሚከሰተውን የጎርፍ አደጋ በዘላቂነት መፍትሔ ለመስጠት ጥናት መጀመሩን ገልጸዋል።
ችግሩን ለመፍታት የምክክር መድረኮች ተዘጋጅተው በወንዙ አቅራቢያ የሚኖሩ ነዋሪዎችን ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዲሰፍሩ እና የተወሰኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን እንዲነሱ መደረጉን ተናግረዋል።

ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ከኦሞ ወንዝ ሙላት ጋር ተያይዞ በአካባቢው በተደጋጋሚ የጎርፍ ማጥለቅለቅ አደጋ ሲከሰት እንደነበር የተናገሩት ኃላፊው፤ አምና ከ79 ሺሕ በላይ አርብቶ አደሮች በወንዙ ሙላት መጥለቅለቅ ከመኖሪያ ቀዬአቸው በመፈናቀላቸው እስከ ዛሬ በጊዜያዊ ማቆያ ስፍራ እንዲቆዩ መደረጉን አንስተዋል፡፡
ቢሆንም ለእርሻ ሥራ በሚል ወደ ቀድሞ ቀዬአቸው በተመለሱት ዜጎች ላይ የአሁን የውሃ ሙላት መጠነኛ ጉዳት ማስከተሉን ገልጸዋል፡፡
በወረዳው ባለፉት 8 ዓመታት በተደጋጋሚ የጎርፍ አደጋ ተከስቶ በ34 ቀበሌዎች የሚኖሩ ከ79 ሺሕ 828 በላይ ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸው አይዘነጋም።
የጎርፍ አደጋው ከነዋሪዎች መፈናቀል ባለፈ፣ የእንስሳት ሞትን ጨምሮ በእርሻ መሬት እና በንብረት ላይ ጉዳት ማስከተሉም የሚታወስ ነው።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ