ጥቅምት 5/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በሕንድ ሕክምና ላይ የነበሩት የቀድሞ የኬንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ በ80 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን ጽ/ቤታቸው አስታውቋል፡፡

የህንድ ጋዜጣ ማትሩብሁሚ ቀደም ብሎ እንደዘገበው፤ በደቡባዊ የህንድ ከተማ ኮቺ የልብ ህመም አጋጥሟቸው በሕክምና ላይ የነበሩ ሲሆን በዛሬው ዕለት ሕይወታቸው ማለፉ ታውቋል።

የኦሬንጅ ዴሞክራቲክ ሙቭመንት መሪ የነበሩት ኦዲንጋ ለኬንያ ፕሬዚዳንትነት 5 ጊዜ ዕጩ ሆነው የተወዳደሩ ቢሆንም ምርጫዎቹን ለማሸነፍ ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ በሁለቱ ምርጫዎች ወቅትም ከፍተኛ ቀውስ በኬንያ ተፈጥሮ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ኦዲንጋ በተለይም ከትውልድ ከተማቸው በምእራብ ኬንያ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ድጋፍ የነበራቸው ሲሆን፤ በቅርቡም ለአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበርነት ቦታ ተወዳድረው ማሸነፍ ሳይችሉ ቀርተዋል።

ለዓመታት የዴሞክራሲ ተሟጋች በመሆን ባከናወኗቸው ተግባራትም፤ ሁለቱን የአገሪቱን ዋና ዋና ለውጦች ማለትም እ.ኤ.አ በ1991 የመድበለ ፓርቲ ዴሞክራሲ ስርዓት እንዲቋቋም እንዲሁም በ2010 አዲስ ሕገ መንግሥት እንዲታተም ረድተዋል።

ከምርጫ 2007 በኋላም ሀገሪቱን ወደ ከፋ የፖለቲካ ቀውስ የገባችበትን ተቃውሞ በመምራት ሥማቸው ይነሳል፡፡

በዚህም ግጭት ወደ 1 ሺሕ 300 የሚጠጉ ሰዎች ተገድለዋል በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።

ኦዲንጋ ህልፈተ ሕይወት ዜናን ተከትሎም፤ የኢፌዴሪ ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ በኢትዮጵያ መንግሥት ሥም ሐዘናቸውን በመግለጽ ነፍሳቸው በሰላም እንድታርፍ ተመኝተዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ