ጥቅምት 5/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማህበር በአንድ አመት ውስጥ ማለትም በ2017 በጀት ዓመት ከ1 ሺሕ 400 በላይ ለሚሆኑና በግንባታው ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሙያዎች ስልጠና መስጠቱን ለአሐዱ አስታውቋል።
በግንባታው ዘርፍ ያሉ ክፍተቶችን ለማስተካከል ብቃት ያላቸው ባለሙያዎችን ማፍራት ላይ በትኩረት እየተሰራበት እንደሚገኝ የገለጹት የማህበሩ ፕሬዝዳንት የሱፍ መሀመድ (ኢ/ር) ናቸው።
በተለይም ባለሙያዎች በስልጠና ያልታገዙ መሆናቸው ለሚደርሱ አደጋዎች እንደአንድ ምክንያት መቀመጡን አንስተዋል።
በዚህም መሠረት ስልጠናው በግንባታ ሳይት ላይ በተደጋጋሚ ስለሚደርሱ አደጋዎችና በሥራ ላይ መደረግ ስላለበት የደህንነት ጥንቃቄ፣ ስላለው አዋጅና መመሪያዎች እንዲሁም ዘርፉ ስላለበት ደረጃ እና ተያያዥ ጉዳዮች መሆኑን አስረድተዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም የአሰልጣኞች ስልጠናም እንዲሁም ከአዲስ አበባ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ጋር በመተባበር መስጠት መቻሉን አንስተዋል።
በቅርቡ በተሰራ ሥራ በአዲስ አበባ ብቻ 3 ሺሕ 500 የሚሆኑ ግንባታዎች ዝቅተኛውን የደህንነት መስፈርት የማያማሉ ሆነው መገኘታቸውን ያስታወሱት ፕሬዝዳንቱ፤ በቀጣይም እነዚህን ግንባታዎች የሚሰሩ ባለሙያዎችን ጨምሮ ለበርካቶች ስልጠናውን ለመስጠት መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።
ማህበሩ በዘርፉ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት ከተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ማህበሩ በአንድ ዓመት ውስጥ ከ1 ሺሕ 400 በላይ በግንባታው ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሙያዎች ስልጠና መሰጠቱን አስታወቀ
