ጥቅምት 5/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የሚተዳደሩ 7 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለሥራ ማስጀመሪያ የሚያስፈልገው 3 ነጥብ 1 ቢልየን ብር ክፍያ ባለመፈጸሙ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ አለመጀመሩን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታውቋል፡፡
የገንዘብ ክፍያ ካልተፈጸመባቸው ፕሮጀክቶች መካከል አያት2 ሎሚ ቀለም፣ ቦሌ አራብሳ 20/80፣ ወታደር ሰፈር፣ በረከት ሰፈር፣ ጀሞ ጋራ እና ፉሪ ሀና 20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ፕሮጀክቶች ይገኙበታል።
በአገልግሎት መስሪያ ቤቱ የአዲስ አበባ ሪጅኖች ኦፕሬሽን ማስተባበሪያ ምክትል ሥራ አስፈጻሚና ከፍተኛ ቴክኒካል አማካሪ አቶ ሸዋይርጋ ላቀው፤ "የመስመር ዝርጋታው፤ የትራንስፎርመር ማስቀመጫ ቦታዎችንና የምድር ውስጥ የኤሌክትሪክ ኬብል ዝርጋታን ያጠቃልላል" ብለዋል፡፡

ክፍያ ተፈጽሞላቸው የሲቪል ሥራቸው ያልተጠናቀቀ 5 ሳይቶች ላይም የዋጋ ልዩነት መምጣቱ ተገልጿል።
ክፍያው ተጠናቆ የሲቪል ሥራቸው ያለቀላቸውን አሥር ፕሮጀክቶች በየግለሰብ ቆጣሪ መግጠም መቻሉን ገልጸው፤ ክፍያው ተፈጽሞ የሲቪል ሥራው ባለማለቁ ምክንያት ቦሌ ቡልቡላ ጨፌ ሳይት ላይ አገልግሎት መስሪያ ቤቱ እቃዎችን ቢያስገባም መግጠም እንዳልተቻለ አብራርተዋል።
አቶ ሸዋይርጋ ላቀው "የዋጋ ልዩነቱ ቢኖርም በተመደበው ገንዘብ ልክ ለመስራት የሲቪል ሥራዎችን መጠናቀቅ እንጠብዋለን" ብለዋል።
በመጨረሻም አገልግሎት መስሪያ ቤቱ፤ በሲቪል ሥራዎች ላይ እና ሌሎችም ኃላፊነት ያለባቸው ተቋማት የድርሻቸውን እንዲወጡና የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታው እንዲፋጠን አስተዋፅኦዋቸውን እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርቧል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ