ሰኔ 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው የመንግሥትን የ2017 የዕቅድ አፈጻጸም አስመልክቶ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ከሰላምና ፀጥታ ጋር በተያያዘ በመንግሥት በኩል እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችን በተመለከተም ከምክር ቤቱ አባላት ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።
በምላሻቸውም፤ "ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሰላምና ፀጥታ ችግር መንስኤ የተሳሳተ የፓለቲካ አመለካከት እንዲሁም የስንፍና ፓለቲካ የወለደው ችግር ነው" ሲሉ ገልጸዋል።
አሁን "በኢትዮጵያ ያሉ የፓለቲካ ሰዎች ሥራ የማይወዱ፣ የማይሰሩ፣ ግብር የማይከፍሉ እና አገልግሎት የማይሰጡ ፓለቲከኞች በዝተዋል" ብለዋል። "እነዚህ ፓለቲከኞች የትኛውን ጥሩ የመተቸትና የመውቀስ ነገር የሚስተዋልባቸው ናቸው" ሲሉም አክለዋል፡፡
"ሌላው 'የኢትዮጵያ የፀጥታ መንስኤ ፍላጎትና እሳቤን በኃይል ማስፈጸም እችላለሁ' የሚለው ሲሆን፤ ከሰሞኑ በዝቋላ አቦ የተፈፀመው ጥቃት ክትትል እየተደረገበት ይገኛል" ብለዋል።
ድህነት፣ ኋላቀርነት፣ ሥራ አጥነት እና የዘረኝነት አመለካከት ተጨማሪ መንስኤዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል። "ስለሆነም ማኅበረሰቡ ታጣቂዎችን ተዉ ማለት ይጠበቅበታል" ሲሉ አሳስበዋል።
በተመሳሳይም የፓለቲከኞችና የጋዜጠኞችን እስር በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ "ኢትዮጵያ ውስጥ ሰው ጋዜጠኛና ፓለቲከኛ ስለሆነ ብቻ አይታሰርም" ብለዋል።
"በእስር ላይ የሚገኙት ጉዳያቸው በፍርድ ቤት የተያዘ መሆኑንና ጥፋት የሌለባቸው አድርጎ ማሰቡ ነገ ችግር ይዞ ይመጣል" ሲሉ ተናግረዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
"የስንፍና ፓለቲካ በኢትዮጵያ ውስጥ የሰላምና ፀጥታ ችግር መንስኤ ነው" ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
"ኢትዮጵያ ውስጥ ሰው ጋዜጠኛና ፓለቲከኛ ስለሆነ ብቻ አይታሰርም" ብለዋል
