ሰኔ 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በቡሩንዲ በጥንቆላ ማጭበርበር የተከሰሱ 6 ግለሰቦች ከገዥው ፓርቲ ጋር ግንኙነት ባለው የወጣቶች ንቅናቄ ቡድን አባላት ተደብድበው መገደላቸውን የአካባቢው ባለስልጣናት ተናግረዋል፡፡
ድርጊቱ ከቡሩንዲ ዋና ከተማ ቡጁምቡራ በስተምስራቅ 10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ጋሳራራ ውስጥ ሰኞ ዕለት መፈጸሙ የተገለጸ ሲሆን፤ በተባበሩት መንግሥታት እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች ዘንድ በሰፊው በሚታወቀው የገዥው ፓርቲ "የኢምቦኔራኩሬ የወጣቶች ንቅናቄ" መፈጸሙን ባለስልጣናቱ ስለመናገራቸው ቲአርቲ ዘግቧል።
እንደ ባለሥልጣናቱ ገለጻ፣ ኢምቦኔራኩሬ የተባለው የወጣቶች ንቅናቄ ቡድን በጥንቆላ ወደ ተከሰሱ አሥር የሚጠጉ ግለሰቦች ቤት በመግባት ጥቃቱን የፈጸመ ሲሆን፤ በሕይወት እያሉ የተቃጠሉ ሁለት ግለሰቦች ጨምሮ ስድስት ሰዎች በዚሁ ጥቃት ተገድለዋል።
"ሌሎቹ በዱላ ተደብድበው ተገድለዋል ወይም በድንጋይ ተወግረው ተገድለዋል" ያሉት ባለስልጣናቱ፤ ይህ አስደንጋጭ እና ሊገለጽ የማይችል የጭካኔ ድርጊት ነበር" ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ሦስት ግለሰቦች ጥቃት የደረሰባቸው ሲሆን፤ ነገር ግን ፖሊስ ጣልቃ በመግባት ከታደጋቸው በኋላ በሕይወት መትረፋቸውን አስታውቀዋል፡፡
የቡጁምቡራ ግዛት አስተዳዳሪ ዴሲሬ ንሴንጊዩምቫ ማክሰኞ ዕለት ከግድያው ጋር በተያያዘ 12 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አረጋግጠዋል።
የኢምቦኔራኩሬ የወጣቶች ንቅናቄ ቡድን ለረጅም ጊዜ ከባድ የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች ክስ ሲቀርብበት ቆይቷል። እንደ ሂዩማን ራይትስ ዎች ያሉ ድርጅቶች በተለይም እ.ኤ.አ. ከ2005 እስከ 2020 ሀገሪቱን በመሩት በቀድሞው ፕሬዝዳንት ፒየር ንኩሩንዚዛ ዘመን፤ ቡድኑ ግለሰቦችን በማሰቃየት እና ያለፍርድ ግድያ በመፈጸም ክስ በተደጋጋሚ ውንጀላ ቀርቦበታል።
የክርስትና እምነት ተከታዮች በብዛት በሚኖሩባት ብሩንዲ፣ ባህላዊ እምነቶች አሁንም ጠንካራ መሆናቸው የሚገለጽ ሲሆን፤ ነገር ግን ምንም እንኳን ማስረጃ ባይኖርም ጥንቆላ በሀገሪቱ በተደጋጋሚ ለሚስጢራዊ ሞት ተጠያቂ መሆኑ ይነገራል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በቡሩንዲ በጥንቆላ ማጭበርበር የተከሰሱ 6 ሰዎች በገዢው ፓርቲ አባላት ተደብድበው መገደላቸው ተሰማ
