ሰኔ 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ከተማ ከ5 ሚልዮን በላይ የትራንስፖርት ተጠቃሚዎች ቢኖሩም እነርሱን የሚያስተናግዱት ተሽከርካሪዎች ቁጥር ከ12 ሺሕ እንደማይበልጥ የከተማ አስተዳደሩ ትራንስፖርት ቢሮ ለአሐዱ ገልጿል፡፡
በቢሮው የሕዝብ ትራንስፖርት ስምሪት አደረጃጃት ዳይሬክተር አሸናፊ ሥዩም፤ "የከተማ አውቶብሶች ዓይነተኛ የትራንስፖርት አማራጭ ሆነዋል" ብለዋል።
በከተማዋ የሚስተዋለውን የትራንስፖርት ችግር ለማቃለል በከተማ አስተዳደሩ ወጪ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ የከተማ አውቶብሶች ግዥ መፈጸሙን ያነሱት አቶ አሸናፊ፤ በቀን ከ1 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ጨምሮ በከተማዋ የትራንስፖት አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
በከተማዋ ከ3 ሺሕ 800 ያላነሱ ኮድ አንድ ተሸከርካሪዎች የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ እና ከ5 ሺሕ 800 እስከ 6 ሺሕ የሚደርሱ ድጋፍ ሰጪ ተሸከርካሪዎች አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙም አስታውቀዋል፡፡
ከእነዚህም መካካል ከ1 ሺሕ የማይበልጡት በተለምዶ ሚኒባስ ተብለው የሚጠሩት ተሸከርካሪዎች መሆናቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙት ድጋፍ ሰጪ ተሸከርካሪዎች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
አንበሳ የከተማ አውቶብስ በቀን 1 ነጥብ 1 ሚልዮን ዜጎችን፤ በቅርቡ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የኤሌትሪክ አውቶብስ በቀን ከ110 ሺሕ በላይ ዜጎችን እያጓጓዘ እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡
ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት በተመለከተ በዚህ ዓመት፤ በቀን 230 እንዲሁም በዓመት 85 ሺሕ 460 የባቡር ትራንስፖርት ምልልሶች መደረጋቸውን የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ያስታወቀ ሲሆን፤ ባለፈው በጀት ዓመት ለ16 ሚሊየን 546 ሺሕ 235 የከተማዋ ነዋሪዎች አገልግሎት መስጠቱን አመላክቷል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በመዲናዋ ከ5 ሚልዮን የሚበልጠውን ትራንስፖርት ፈላጊ የሚያስተናግዱ ተሽከርካሪዎች ከ12 ሺሕ እንደማይበልጡ ተነገረ
በቀን ከሚጓጓዙ 4 ሚልዮን ሰዎች መካከል 1 ነጥብ 1 ሚልዮን በላይ የሚሆኑት የከተማ አውቶብስ ተጠቃሚ ናቸው ተብሏል
