ሰኔ 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ከ5 ዓመታት በፊት የሴት ልጅ ግርዛትንና ያለዕድሜ ጋብቻን ለማስቀረት በሀገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ የተደረገው ፍኖተካርታ (የ5 ዓመት የድርጊት መርሃ ግብር) የጊዜ ገደቡ ማብቃቱን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ለአሐዱ አስታውቋል።

ይህንን ተከትሎም በአሁኑ ሰዓት ግምገማ እየተካሄደበት እንደሚገኝ የገለጹት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሴቶች ጥቃት ጥበቃና መከላከል ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ዘካሪያስ ደሳለኝ፤ ፍኖተካርታው በሴቶች ላይ የሚፈፀመውን ድርጊት ከመቀነስ አንፃር የሚያግዝ እንደሆነ ተናግረዋል።

አሐዱም "በፍኖተ ካርታው ጥናት መሠረት በኢትዮጵያ የሴት ልጅ ግርዛትና ያለዕድሜ ጋብቻ አሁን ምን ደረጃ ላይ ይገኛል? የተገኙ ውጤቶች ምን ይመስላሉ?" ሲል ጠይቋል።

ከፍተኛ ባለሙያው በምላሻቸው በግምገማው መሠረት የተገኙ ውጤቶች ታይተው፤ በዛ መሠረት ፍኖተካርታው ይራዘም ወይም ደግሞ ይሻሻል የሚለው ውሳኔ እንደሚሰጥበት ተናግረዋል።

በመሆኑም የተገኘው ውጤት ከግምገማው በኋላ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ይፋ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

በተያያዘም ከሴት ልጅ ግርዛትና ያለዕድሜ ጋብቻ ባሻገር አጠቃላይ የሴት ልጅ ጥቃትን ለመቆጣጠርና ለማስቀረት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተጠናከረ ሥራ እየተሰራበት እንደሚገኝ አንስተዋል።

ይህንን በሚመለከት የተዘጋጀው ስትራቴጂም ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ