ዲሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ ፓርቲ ምንም ዓይነት የጦር ክንፍ እንደሌለው አስታውቋል፡፡

ትግራይ ክልል ውስጥ የመመስራች ጉባኤውን ማድረግ አለመቻሉ የሚገልፀው ፓርቲው፤ በትግራይ ያለው ፅሕፈት ቤቱ ጭምር መሰበሩን ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ ፓርቲ ጊዜያዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምዝገባ ፈቃድ በግንቦት ወር ላይ መስጠቱ ይታወሳል፡፡

ቦርዱ በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011ዓ.ም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲ ጊዜያዊ የምዝገባ ፈቃድ ሰጥቶታል፡፡

Post image

የፓርቲው መስራቾች በአብዛኛው በምርጫ ቦርድ ዕውቅና የተነፈገው የህወሓት አባላት ሲሆኑ፤ በከፍተኛ አመራርነት ጭምር ሲያገለግሉ የነበሩ አባላት ይገኙበታል፡፡

ይሁን እንጂ በውስጣዊ መካፋፈል የተነሳ የፓርቲው አባላት የራሳቸውን "ዲሞክራሲ ስምረት ትግራይ" ሲሉ አዲስ ፓርቲ አቋቋመዋል፡፡

ህወሓት በትግራይ ክልል የፕሪቶሪያው የሰላም ሰምምነት እንዲፈርስ "ፅምዶ" በሚል ከኤርትራ መንግሥት ጋር በመመሰረት እየሰራ በመሆኑ፤ ከድርጅቱ ለመነጠላቸው አንዱ ምክንያት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ፓርቲው ጊዚያዊ ዕውቅና ከተሰጠው ጊዜ አንስቶ፤ በሦስት ወር ውስጥ የመስራች ጉባኤ ማድረግ የሚገባው ቢሆንም እንዳልተሳካለት ይገለጻል፡፡

ፓርቲው ነሐሴ 17 ቀን 2017 ሊያካሂደው ያሰበውም ጠቅላላ ጉባኤ በክልሉ ጊዚያዊ አስተዳደር በመታገዱ፤ ጉባኤውን አራዝሞት እንደነበርም ይታወሳል፡፡

ጊዜያዊ አስተዳደሩም ይህንን ጉባኤ እንዳያደርጉ የአሻንዳ እና አይነዋሪ በዓላትን ምክንያት በማድረግ የፀጥታ ሽፋን እንደማይደረግ ተገልጾላቸው ጉባኤውን ማድረግ ሳይችሉ መቆየታቸውን አስታውቀዋል፡፡

ትግራይ ክልል ውስጥ የመመስራች ጉባኤውን ማድረግ አለመቻሉ የሚገልጸው ፓርቲው፤ በትግራይ ያለው ፅህፈት ቤቱ ጭምር መሰበሩን ያነሳል፡፡

ይሁን እንጂ ፓርቲው የተሰጠው ሦስት ወር ከመጠናቀቁ አስቀድሞ፤ በአዲ አበባ በዛሬው ዕለት የመመስረቻ ጉባኤውን አስጀምሯል፡፡

Post image

በጉባኤው መከፍቻ ላይም በርካታ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎችን ጨምሮ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እና ፖለቲከኞች ተገኝተውበታል፡፡

የፓርቲው መሰራች እና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የምስራቅ አፍሪካ አማካሪ አቶ ጌታቸው ረዳ በጉባኤው ላይ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡

በንግግራቸውም በህወሓት ውስጥ በተፈጠረው ችግር ምክንያት አዲስ ፖርቲ ለመመስረት መገደዳቸውን ገልጸዋል።

አቶ ጌታቸው በትግራይ ጉባኤውን ለማድረግ ፍላጎት የነበረ ቢሆንም፤ በክልሉ ያለው "ስርዓት አልበኝነት ጫፍ የደረሰ" በመሆኑ ማካሄድ አለመቻላቸውን ገልጸዋል።

Post image

በትግራይ ክልል መንቀሳቀስ እንዳይችል የተለያየ ሰያሜ እየተሰጠው እንደሆነ የሚገልጸው ፓርቲው፤ ከታጠቁ ኃይሎች ጋር ጭምር ትስስር እንዳለው እንደሚገለጽ አንስቷል፡፡

በተጨማሪም እስከ ወረዳ ድረስ በትግራይ ውስጥ የስምረት ፓርቲ ከተገኘ እስከመታሰር እየደረሱ መሆኑንም ይገልጻል፡፡

አቶ ጣዕመ አርዓዶም በዲሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ ፓርቲ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ምክትል አስተባባሪ ናቸው፡፡

አስተባባሪው እንደሚገልጹት ፓርቲው ጉባኤውን በትግራይ ክልል ማከናወን አስቸጋሪ ሁኔታ በመኖሩ፤ በአዲስ አበባ ለማድረግ ተገዷል፡፡

Post image

ዲሞክራሲ ስምረት ትግራይ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል የሚሰራ ፓርቲ መሆኑን የሚያነሱት አቶ ጣዕመ፤ ነገር ግን የተለያዩ የህወሓት አመራሮች ሀሰተኛ መረጃ እንደሚያወጡባቸው ይገልጻሉ፡፡

ፓርቲው በትግራይ ክልል ያለውን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ከሌሎች ፓርቲዎች እና የሚመለከታቸው አካላት ጋር ጭምር እንደሚሰራ ያስረዳሉ፡፡

Post image

ነገር ግን በ"ሐራ መሬት" ያሉ አካላት ሀሳብ የሚደግፉ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ ሰላማዊ ፖለቲካ ትግል መንቀሳቀስ ባለመቻላቸው ተገደው ወደ ጫካ የወረዱ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡

በትግራይ ከልል ያለው ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰና ነገሮችን ወደ ግጭት እንዳያመሩ የሚያሰጋበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

በተለይም በምርጫ ቦርድ የተሰረዘው ህወሓት በክልሉ ከኤርትራ መንግሥት ጋር የፈጠረው ጥምረት ብዙዎችን ስጋት ውስጥ ጥሏል፡፡

በተቃራኒው ደግሞ ቀድሞ የክልሉ ወታደራዊ ኃላፊና አባላት የነበሩ በርከት ያሉ የጦር አባላት "ሐራ መሬት" ወይም "ነፃ መሬት" ብለው ወደ ጠሩት አካባቢዎች ከወረዱ ቆይተዋል፡፡

ይህንን እራሱን "የትግራይ የሰላም ሠራዊት" ብሎ የሚጠራው አካል የዲሞክራሲ ስምረት ትግራይ ክንፍ እንደሆነ የህወሓት የጦር አመራሮችን ጨምሮ ሌሎችም ይገልጻሉ፡፡

ይህንን በሚመለከት ጥያቄ ያነሳንላቸው አቶ ብርሐነ ገብረየሱስ ፓርቲው የአደረጃጀት ኮሚቴ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ፤ "ይህ ፍፁም ሀስት ነው" ይላሉ፡፡

እነዚህ አባላት እያደረጉት ትግልን የሚደግፉ መሆኑን ያነሱ ሲሆን ይሁን እንጂ እኛ በትጥቅ ትግል አናምንም በሰላማዊ መንገደድ ብቻ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

Post image

ዲሞክራሲ ስምረት ተግራይ የመመስረቻ ጉባኤው የምርጫ ቦርድ ታዛቢዎች በተገኙበት እየተካሄደ ሲሆን፤ አመራሮቹን ይመርጣል ተብሎም ይጠበቃል፡፡

አቶ መለስ አለም ብልፅግናን በመወከል በጉባኤው ላይ የተገኙ ሲሆን፤ ዲሞክራሲዊ ስምረት ትግራይ ለምስረታ በመብቃቱ ደስታቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ አዲስ የፖለቲካ መስመር ውስጥ መግባቷን ማሳያ መግባባት እና መቀራረብ የሚችሉ ሀሳቦችን ወደ አንድ በመማጣት ፖርቲዎች ወደ አንድነት አምጥቶ መስራት ማሳያው ነው ብለዋል።

Post image

ብልፅግና ፖርቲ የሀሳብ ልዩነቱን ጠብቆ ከዲሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ ጋር በአጋርነት ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑንም አቶ መለስ ተናግረዋል።

ዲሞክራሲ ስምረት ትግራይ ፓርቲ አሁን ላይ በክልሉ ያለውን ችግር ከሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ጋር ሆኖ ለመፍታት እና አማራጭ ሃሳብ ለመሆን በማሳብ የተቋቋመ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ፓርቲው ትግራይ የፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ተተግብሮ ወደ መደበኛ ሕገ-መንግሥታዊ ስርዓት እንድትመለስ እንሚሰራም በጉባኤው ወቅት ገልጿል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ