ሕዳር 2/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ከ20 በላይ ሀገራት በሱዳን እየተፈፀመ ያለውን የንፁሃን ግድያ አወግዘው፤ ሁለቱ ጦረኛ ጄነራሎች የንፁሃን ደም ማፍሰሳቸውን ማቆም አለባቸው ሲሉ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
ከ20 የሚበልጡ ሀገራት የተውጣጡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና ከፍተኛ ባለስልጣናት በሱዳን የተፈመውንና አሁንም የቀጠለውን የንፁሃን ሰዎች ግድያና አስገዳጅ መፈናቅል አሰቃቂ እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ሕግ ጥሰት፤ የሱዳን ጦር መሪ ጄነራል አብድል ፈታህ አልቦረሃንና ተቀናቃኛቸው ጄነራል ሃምዳን ደጋሉ ወይም በቅጥል ስማቸው ሂሜቲ ኃላፊነቱን ይወስዳሉ ሲሉ ክስ አቅርበዋል።
በሰላማዊ ሰዎች ላይ ስልታዊ ጥቃት በሚሰነዝሩ ጥቃቶች የተገደሉና አሁን የሞት አፋፍ ላይ በሚገኙ ሱዳናዊን የተሰማቸውን ጥልቅ ስጋት የገለጹት የሀገራቱ ሚኒስትሮችና ባለስልጣናት፤ ይህ ጥቃት መቆም አለበት ስለማለታቸውን ዘጋርዲያንና ሲኤን.ኤን.ኤን ዘግበዋል።

በተለይ የኤልፍሽር ከተማ በፈጥኖ ደራሽ ሃይሎች ቁጥጥር ሥር መውደቋ፣ በሰሜን ዳርፉር እና በኮርዶፋን አካባቢ የሚካሄደው ጦርነት እየተባባሰ መምጣቱ እንዲሁም፤ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸመው ስልታዊ እና ቀጣይነት ያለው ጥቃት አሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉ ሚኒስትሮቹ እንዳሳሰባባቸው ገልጸዋል።
በሰላማዊ ሰዎች ላይ ሆን ተብሎ ማነጣጠር፣ ዘርን መሰረት ያደረጉ የጅምላ ግድያዎች፣ ከግጭት ጋር የተያያዘ የፆታ ጥቃት፣ ረሃብ እንደ ጦርነት መሳሪያ መጠቀም እና የሰብአዊ አቅርቦትን ማደናቀፍ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግን በአጸያፊ መልኩ መጣስ ነው ሲሉ ገልጸውታል።
እንዲህ ያሉት ድርጊቶች ከተረጋገጡ የጦር ወንጀሎች እና በዓለም አቀፍ ሕግ በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን የሚያካትቱ ናቸው ብለዋል ሚኒስትሮቹ በጋራ ባወጡት መግለጫ።
ሚኒስትሮቹ እና ባለሥልጣናቱ ድርጊቱ በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቀው፤ "ለሱዳን ሕዝብ ጥበቃ እና ፍትህ መስጠት ሕጋዊ ግዴታ ብቻ ሳይሆን አስቸኳይ የሞራል ግዴታም ነው" ሲሉ አሳስበዋል።
በተጨማሪም "የተስፋፋው ረሃብ ሊታገስ የማይችል ነው" ሲሉ የገለጹት ሚኒስትሮቹና ባለሥልጣናቱ፤ የዓለም ምግብ ፕሮግራም (ደብሊውኤፍፒ)፣ የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) እና ሌሎች የሰብዓዊ ድርጅቶች ዕርዳታን በነፃ እንዲያደርሱ አሳስብዋል።
በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ ቁጥር 2736 መሠረት ለሲቪሎች በአስተማማኝ ሁኔታ የሰብዓዊ አቅርቦት እንዲተላለፉ እና ዕርዳታውን በአስቸኳይ እንዲመቻች በመጠየቅ "ሁሉም ተፋላሚ ኃይሎች ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ሕግን ማክበር አለባቸው" ብለዋል።

ተፋላሚ ኃይሎቹ የተኩስ አቁም እና የሦስት ወር የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።
"ለሀገር ሉዓላዊነት፣ አንድነት እና የግዛት አንድነት ሱዳናዊያን ያለ ውጫዊ ጣልቃ ገብነት በሰላም፣ በክብር እና በፍትህ የመኖር መብታቸውን እንደግፋለን" ብለዋል ከ20 ሀገራት የተውጣጡት ሚኒስትሮች።
የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ላይ ክስ ካቀረቡ የሀገራት ሚኒስትሮች መካከል ካናዳ፣ ስፔን፣ እንግሊዝ፣ ኖርዌይ፣ ጀርመን፣ አየርላንድ፣ ስዊድን፣ ኦስትሪያ፣ ክሮኤሺያ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ፊንላንድ፣ ፖላንድ እና ስዊዘርላንድ ይገኙበታል።
ሚኒስትሮቹ እና ባለሥልጣናቱ "የሱዳንን ተግዳሮቶች ሊፈታ የሚችለው ሰፊና ሁሉን አቀፍ የሱዳን የፖለቲካ ሂደት ብቻ ነው" ሲሉ ገልጸው፤ ሁሉም ኃይሎች ወደ ድርድር እንዲመጡ አሳስበዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ