ሕዳር 2/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮጵያ ረዥም ዘመን የጸና የሀገር-መንግሥት ሥርዓት፣ የዳበረ ጽሑፍና ባህል ያላት ጥንታዊት ሀገር ብትሆንም፣ የፖለቲካ ልሂቃንና የአካዳሚ ምሁራን በሀገረ-መንግሥት ምስረታዋ፣ በታሪኳና በፖለቲካ አወቃቀሯ ላይ የጋራና አንድነት ባለው ትርክት ላይ አይስማሙም።

ይህ አለመግባባት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተናረ፤ የጎሳና የብሔር መልክ እየያዘ ሀገሪቱን ለግጭትና ውዝግብ መድረክ አድርጓታል።

ይህን የትርክት ልዩነት ለማጥበብ ምሁራን በጥናት ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ቢያቀርቡም፤ ሙከራዎቹ በአብዛኛው በፖለቲካ ሥልጣን በሚይዙ ኃይሎች ውድቅ ስለሚደረጉ ከወረቀት አልፈው ተግባራዊ ለውጥ ሳያመጡ መክነዋል።

በቅርብ ዓመታት በተለያዩ አካባቢዎች የታዩ ግጭቶችና በዘር ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች በአንድ ወይም በሌላ መልኩ የዚህ የትርክት ልዩነት ውጤት መሆናቸው ይነሳል።

የኢትዮጵያ ሙያ ማኅበራት ሕብረት ይህንን አሳሳቢ ጉዳይ በመመልከት፤ ከሰሞኑ የተለያዩ ምሁራንን በመጋበዝ በታሪክና ትርክት ዙሪያ ሰፊ ውይይት አድርጓል።

Post image

በውይይቱ ላይ ዋናውን የውይይት ጽሑፍ ያቀረቡት ታዋቂው የታሪክ ተመራማሪ ኤመሬተስ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ፤ ማንኛውም ታሪክ የራሱ ችግር እንደሚኖረውና ይህም በሰዎች የታሪክ ድምዳሜ ላይ ተጽዕኖ እንደሚፈጥር ይገልጻሉ።

ለዚህም ነው ታሪክ በተቻለ መጠን አካታችና ሚዛናዊ መሆን እንደሚገባው አጽንዖት የሰጡት።

ፕሮፌሰር ባህሩ የኢትዮጵያ ታሪክ በአብዛኛው በሰሜኑ አካባቢ ላይ ብቻ ያተኮረ እንደነበር የገለጹ ሲሆን፤ ከ60ዎቹ ወዲህ የደቡብን ታሪክ ለመካተት ጥረት ቢደረግም፣ አብዛኛው ለሕትመት ሳይበቃ መቅረቱን ይናገራሉ።

Post image

ደቡብ ሲባል በአጠቃላይ የኦሮሞው፣ የጉራጌውና በአስተዳደር ከሰሜኑ የተለየ የነበረው ሁሉ መሆኑን ልብ ይባል ብለዋል።

አሁንም የኢትዮጵያ ታሪክ በገዢ ትርክት ላይ የቆመ መሆኑን የሚናገሩት ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ፤ ይህ አካሔድ የመጣው ከዐፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ መሆኑን ይገልጻሉ። በተለይም የመጨቆን ስሜት ያላቸው እንዲሁም አሁን ላይ ተዘንግተናል የሚሉ ብሔረሰቦች መፈጠራቸው ለዚህ ማሳያ ነው ይላሉ።

ተመራማሪው በታሪክ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው የኢትዮጵያ የተማሪዎች ንቅናቄ የነበረውን ሥርዓት በመለወጥ ለውጥ ቢያመጣም፣ ከብሔር ጥያቄ ጋር በተያያዘ ያመጣው የመፍትሔ ሐሳብ ከማቀራረብ ይልቅ የሚያራርቅ ጉዳይ መፍጠሩን ይገልጻሉ።

ይህንን ችግር ለመፍታት የኢትዮጵያ ታሪክ ባለሙያዎች ማኅበር ሰፊ ሥራዎች ማድረጉን ጠቅሰዋል።

ማኅበሩ እንደገና የተቋቋመው የካቲት 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም በዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የነበረ ቢሆንም በደርግ ዘመነ መንግሥት እንዲፈርስ ተደርጎ እንደነበር አስታውሰዋል።

ይህ ማኅበር በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ያሉ ተሳሳቱ ትርክቶችን ለማረም በሚል ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመሆን የሰራቸው ሥራዎች አሉ።

ከእነዚህም መካከል፣ ታግዶ የነበረውና የማንኛውም ዲፓርትመንት ተማሪ የኢትዮጵያን ታሪክ እንዲማር የሚያደርገው የመጀመሪያ ዓመት የትምህርት ኮርስ እንደገና እንዲጀመር ማድረጉን ፕሮፌሰር ባህሩ ገልጸዋል።

Post image

በተጨማሪም፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ዙሪያ አከራካሪ የሆኑ ታሪኮችን በማጥራት ላይ ማለትም አካታችነት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል።

ታሪክ ራሱ ተፈጥሯዊ ችግር የለበትም የሚሉት ምሁራን፣ ችግሩ የሚመጣው ታሪክን ለራሳቸው ጥቅም ለማዋል የሚሞክሩ ፖለቲከኞች መሆናቸውን ይናገራሉ። ፖለቲከኞች ታሪክን በሚፈልጉት መንገድ በመተርጎምና በመነዛዛት ለግጭትና ለጦርነት ሲዳርጉ መቆየታቸውም ይገለጻል።

አቶ አያሌው ዘገየ፣ የዲያሎግ ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር፣ ፖለቲከኞች ታሪክን መቀስቀሻ ማድረጋቸው ሌላ ችግር መሆኑን ያነሳሉ። በመሆኑም ይህ ሁኔታ ላለንበት ችግር አባባሽ በመሆኑ፣ አንዱ ሌላውን ትቶ የሚሄድበት አካሔድ እንደማያዋጣ መረዳት ያስፍልጋል ሲሉ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

Post image

አቶ አያሌው አክለውም፤ የታሪካችንን መነሻ ማወቅ ለጥሩ መድረሻችን ግብአት ነውና፤ ታሪክን ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋላችንን ትተን ለሩቁ በጎ ዓላማ ልንጠቀምበት ይገባል ብለዋል።

"ለምናደርገው ሁሉ ብሔራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ" እንደሚገባም አጽንዖት ሰጥተው፤ የኢትዮጵያ መገለጫ የሆነ የጋራ ነገር እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።

ችግራችን የቆየ ከመሆኑም በላይ፤ አሁን ያሉትንም የጋራ ትርክት መፍጠር የችግሮቻችን መፍቻ ቁልፍ መሆኑን ተናግረዋል።

ታሪክ ዛሬን እንድንረዳ፣ ማንነታችንን እንድናውቅና መቻቻልን ለማምጣት እንደሚጠቅም ይነሳል። ታሪክ ማለት ከመጀመሪያው እስከ አሁን ድረስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በግለሰብ ወይም በቡድን ደረጃ የከወነው ጥሩም መጥፎም የተግባር ክንውን ድምር መዝገብ ነው።

ታሪክ ልማትም፣ ሀገርም፣ ሕዝብም የትውልድ ቅብብሎሽ ውጤት እንጂ፤ በአንድ ጀንበር የተፈጠረ አይደለም። በመሆኑም ትላንትና ዛሬን አስታርቆ የጎደለውን ሞልቶ ለመጪው ትውልድ የማስተላለፍ ኃላፊነት እንዳለብን ይነሳል።

ከታሪክና ከሥልጣን ሽሚያ ወጥቶ፣ አገራዊ ነፃ ተቋማትን ገንብቶ፣ በጠራ ርዕዮተ-ዓለም ብቻ የምትመራ የሁላችን የሆነች ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መገንባት የሁሉንም ትብብር እንደሚጠይቅ ይገለጻል።

የኢትዮጵያ ሙያ ማኅበራት ሕብረት በሀገሪቱ ያሉ ማኅበራት ሁሉ ችግር ፈቺ ጉዳዮች ላይ "ለኢትዮጵያ ይበጃል" የሚሉትን እንዲሰሩ ለማድረግ በማለም የተቋቋመ ነው።

የማኅበሩ መስራች ከሆኑት መካከል አርቲስት ደሳለኝ ኃይሉ፣ ይህንን ማኅበር ለማቋቋም ከፍተኛ ፈተና ማለፉን ይገልጻል።

Post image

ከብሔርና ከሃይማኖት ጋር ያሉ ችግሮችን ከመፍታት በፊት የሙያ ማኅበራትን ማቋቋም አስፈላጊ መሆኑን ማመናቸውን ይናገራሉ።

የታሪክ ተመራማሪዎች የቋንቋ ጥናት፣ የአርኪኦሎጂ ምርምርና የጂኦግራፊያዊ ጥናቶችን መሠረት ያደረጉ ወጥ የታሪክ መረጃዎችን እንዲያቀርቡ ማድረግ፤ የታሪክ አተያይና አረዳዳችንን የሚቃኙ ወጥ የሆነ የጋራ ግንዛቤ በትምህርት ማዕከሎቻችን እንዲሰጥ ማድረግ ይገባል፡፡

በተለይም የታሪክ ትምህርት እንደ ዋና ትምህርት ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ መሰጠቱ ጠቃሚ መሆኑ ይጠቀሳል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ