ጥቅምት 4/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ትምህርት እና ሥልጠናን መሠረት ያደረገ አዲስ ፖሊሲ በዚህ ዓመት ተግባራዊ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

የፖሊሲው ዋና ዓላማ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ የሰው ኃይል መፍጠር፣ በሀገሪቱ የሚገኙ ወጣቶችን ጉልበት በአግባቡ መጠቀም የሚያስችል አሰራር መዘርጋት ነው ተብሏል።

በሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ስልጠና የተቋማት አቅም ግንባታ መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሙሁዲን ባቡክ፣ "አዲሱ ፖሊሲ ሲተገበር ሥልጠናን ከተወዳዳሪነት ጋር በማቀናጀት የገበያውን ፍላጎት መሠረት በማድረግ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆነ የሰው ኃይልን ያዘጋጃል" ሲሉ ለአሐዱ ተናግረዋል።

"በፖሊሲው መሰረት የዲጂታል ክህሎት የስልጠናው ዋነኛ አካል እንዲሆን ሥራዎች እየተሰሩ ነው" ያሉት መሪ ሥራ አስፈጻሚው፤ ጥናቱን መሠረት በማድረግ እንዲዘጋጅ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በቴክኒክ እና ሙያ ሰልጥነው የሚወጡ ተማሪዎች ለሀገር ውስጥ ኩባንያዎች ብቁ እንዲሆኑ ብቻ ሳይሆን፤ በዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ተፈላጊና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማድረግ የፖሊሲው ትኩረት ነው ተብሏል።

ፖሊሲውን በያዝነው በጀት ዓመት መተግበር እንዲቻል ባለፉት 3 ወራት 2 ሺሕ ለሚደርሱ ተቋማት ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ