ጥቅምት 3/2018 (አሐዱ ሬዲዮ)z"ዩኒቨርሲቲዎች የተቀመጡ መሥፈርቶችን ማሟላት ካልቻሉ ሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ይደረጋሉ" ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ

"ይህ አካሄድ አዳዲስ ዩኒቨርስቲዎችን ከሥራ ውጪ ሊያደርጋቸው ይችላል" የትምህርት ባለሙያዎች

ባለፉት 4 ዓመታት ገደማ ሀገሪቱ የምትከተለው የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ዩኒቨርስቲዎች የሚቀበሉት የተማሪ ብዛት እንዲቀንስ አድርጓል።

ከሰሞኑ ደግሞ የትምህርት ሚኒስቴር ከመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የ2018 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ቁልፍ ተግባራት የፊርማ ሥነ-ሥርዓት ባለፈው ሳምንት አርብ መስከረም 30 ቀን 2018 ዓ.ም. አካሂዷል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ እንደ ከዚህ ቀደሙ "አንዴ ዩኒቨርሲቲ ተከፍቷልና በዚሁ ይቀጥላል" የሚባል አሰራር እንደማይኖር ተናግረዋል።

ተማሪዎች በማይመርጧቸው ዩኒቨርሲቲዎች ላይ መንግሥት በቢሊዮን የሚቆጠር በጀት ማውጣት ተገቢ አይሆንም ብለዋል።

ከሰሞኑ ደግሞ ሚኒስትሩ በሚቀጥሉት ዓመታት ተማሪዎች በመረጡት ዩኒቨርሲቲ መማር እንደሚጀምሩ አስታውቀዋል።

በተጨማሪም፤ በተማሪዎች መመረጥ ያልቻሉ ዩኒቨርሲቲዎች ለሌሎች አገልግሎቶች ሊውሉ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።

Post image

ይህንን አስመልክቶ ሐሳባቸውን ለአሐዱ የሰጡት የትምህርት ባለሙያው ሳሜኤል አሰፋ (ዶ/ር)፤ ይህ ዓይነቱ አሠራር በተለያዩ ሀገራት ልምድ ሲሆን በአሜሪካና በአውሮፓ ሀገራት ተመሳሳይ አሰራር እንዳለ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ አዲሱን አሰራር በአንድ ጊዜ ተግባራዊ ለማድረግ አስቸጋሪ እንደሆነ አንስተዋል። ለተማሪዎች የፈለጉት ቦታ እና ትምህርት መማር መቻላቸው ግን በጎ ጎን አለው ይላሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ ይህ አሰራር አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎችን ከማባከን በላይ ከሥራ ውጪ ሊያደርጋቸው እንደሚችልም አንስተዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሂሳብ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ሳሙኤል አሰፋ (ዶ/ር)፤ ይህ ሂደት ለ10 ዓመት ያላነሰ ጊዜ ውስጥ ቀስ በቀስ መተግበር ነበረበት ይላሉ።

ከዚህ ቀደም በመንግሥት አቅጣጫ ምደባ የሚደረግላቸው የትምህርት ዓይነቶች የሚመርጧቸው ሊያጡ ይችላሉ የሚል ሥጋታቸውንም ገልጸዋል።

በመድረኩ ዩኒቨርሲቲዎች ለራሳቸው ሲሉ የመማር ማስተማር ሥርዓታቸው ጥራት ያለው እንዲሆን መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም ተነስቷል።

ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ከዚህ በፊት የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚጠበቅባቸውን መስፈርቶች ማሟላት ካልቻሉ ራሳቸውን ሰፋ ወዳለ ሁለተኛ ደረጃ ወይም አዳሪ ትምህርት ቤቶች የሚለውጡበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል መናገራቸው የሚታወስ ነው።

የቀድሞው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት እና የትምህርት አማካሪ መንገሻ አድማሱ (ፕ/ር) "ዩኒቨርሲቲዎች የሚፈልጉትን ያህል ተማሪ የሚያገኙ ከሆነ ውሳኔው የተሻለ ይሆናል" ይላሉ።

አሁን ካለው የሀገሪቱ የጸጥታ ሁኔታ አንፃር ግን ተማሪዎችና ቤተሰቦች በአካባቢያቸው ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች መማርን መምረጣቸው እንደማይቀር ይገምታሉ፡፡

የኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስቴር የሚያስተዳድራቸው የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት (ዩኒቨርሲቲዎች) ቁጥር ከ47 በላይ ሆኗል።

ይህ ቁጥር የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ መከላከያ ሠራዊት እና ፌዴራል ፖሊስ ያቋቋሟቸውን ዩኒቨርሲቲዎች አይጨምርም።

የመንግሥትና የግል ዩኒቨርሲቲዎች ቁጥር መጨመር ከተማሪ ቁጥር መጨመር ጋር በተያያዘ አድናቆት ቢቸረውም፣ የ"ጥራት ጉድለት አለበት" በሚል ከፍተኛ ትችት ይቀርብበታል።

ተቋማቱ ስኬታማና በራሳቸው የሚተማመኑ ዜጎችን ለማፍራት "ሥርዓተ ትምህርታቸው ከሀገር በቀል የዕውቀት ሥርዓት ጋር የተሳሰረ ሊሆን ይገባል" የሚል ሙግት ቀርቧል።

ባለሙያዎች በተማሪዎች ቁጥር እና በመሠረተ ልማት ግንባታ ዕድገት ቢኖርም ውጤቱ ለመንግሥትና ለዜጎች "አመርቂ አይደለም" ሲሉ ይተቻሉ። ይህ ደግሞ "ተቋማቱ የሚሰጡት ትምህርትና ሥልጠና ከኢንዱስትሪው ፍላጎት ጋር ምን ያህል የተጣጣመ ነው?" የሚል ጥያቄ ያስነሳል።

ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ በተካሄደው ፎረም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በትምህርት ዘመኑ በእቅድ የሚያከናውኗቸውን ቁልፍ ተግባራት አፈፃፀም በመከታተል፤ ለሚከሰቱ ክፍተቶች አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግና ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሚገባቸው ተገልጿል።

ተቋማቱ ስለ ተማሪያቸውና አጠቃላይ የትምህርት ሥርዓት አፈፃፀም ትክክለኛ መረጃ ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ካላቀረቡ፤ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶችን ጨምሮ አመራሮች ከኃላፊነታቸው እንደሚነሱ ተገልጿል።

በጉዳዩ ላይ ሐሳባቸውን የሰጡት የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጀማል የሱፍ፤ ባለው ውስን ሀብት ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ጉዳዮች ቅድሚያ በመስጠት ሥራዎች እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በተጨማሪም፤ በዩኒቨርሲቲዎች በተመደበው በጀት አቅም መፈፀም የሚችሉ ኢንቨስትመንቶችን ለመሥራት የታሰበ መሆኑን ገልጸዋል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አስራት አፀደወይን ዩኒቨርሲቲው ከተቀመጠለት መስፈርት አንፃር የሚቀሩት ጉዳዮች በርካቶች ናቸው ብለዋል።

የተሰጡትን መስፈርቶች ለማሳካት አሁን ካለው የተሻለ አፈፃፀም ለማስመዝገብ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። እንደ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምር ተቋምነት በምርምር ረገድ የሚቀሩ በርካታ ሥራዎች መኖራቸውን አንስተው፣ ይህንን ለማስተካከል እንደሚሰሩ ጨምረው ገልጸዋል።

የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፋና ሐጎስ በበኩላቸው በክልሉ በነበረው ጦርነት ምክንያት ወደ ኋላ የቀሩባቸው ጉዳዮች መኖራቸውን ያስታውሳሉ። በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው በምርምር ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ገልጸው፣ በቀጣይ ደግሞ ራስ ገዝ ሂደት እንደሚጀምር ተናግረዋል።

ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች በቀጣይም አጭር ጊዜ ውስጥ በሀገሪቷ የትምህርት ጥራት ማረጋገጫ ሥርዓት እንደሚመዘኑ ተገልጿል።

መምህራን፣ ተማሪዎች፣ ምሩቃን ያሉበትን ደረጃና ሌሎች አስፈላጊ መረጃዎችን በትክክል ማቅረብ ከዩኒቨርሲቲዎች እንደሚጠበቅ ተገልጿል። ይህንን ማድረግ የማይችል የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ተጠያቂ እንደሚሆን በፎረሙ ወቅት ተነስቷል።

የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኮራ ጡሹኔ፤ የአፈፃፀም ስምምነቱ ውል የክትትልና ግምገማ ሥርዓት እንዳለው ጠቅሰዋል።

Post image

ዩኒቨርሲቲዎች በተፈራረሙበት ቁልፍ የውጤት አመልካቾች መሰረት በተልዕኳቸው ላይ አትኩረው እንዲሰሩ አሳስበዋል። በተጨማሪም፤ ዩኒቨርሲቲዎች የመማር ማስተማር ሂደቱና የትምህርት ጥራት ላይ ትኩረት አድርገው መሥራት እንደሚገባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።

በመንግሥት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከጥራት አንፃር ግምገማ እንደሚደረግ የተገለጸ ሲሆን፤ መስፈርቱን የማያሟሉ ከሆነ ዩኒቨርሲቲዎቹ እንደሚዘጉ ተገልጿል።

በዚህም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የተቀመጡ መስፈርቶችን ማሟላት ካልቻሉ የሚኖራቸው ጥቅም እንደሚገመገም የትምህርት ሚኒስቴሩ አንስተዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ