ጥቅምት 6/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በመጀመሪያው ፈተና የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ያላስመዘገቡ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የድጋሚ እድል የሚያገኙበት የ'ሪሜዲያል' ፈተና የዚህ ዓመት ውጤት ላይ በግል ትምህርት ተቋማት እና ትምህርት ሚኒስቴር መካከል አለመግባባት መፈጠሩን የኢትዮጵያ የግል ከፍተኛ ትምህርት፣ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት ማህበር ገልጿል፡፡

‎ማህበሩ "በትምህርት ሚኒስቴር የተቀመጠው የቁጥር መጠን ከማለፊያ መቶኛ ጋር አለመጣጣሙ ግራ መጋባትን ፈጥሯል" በማለት ቅሬታውን ሲያቀርብ፤ ሚኒስቴሩ በበኩሉ ቁጥሩ የተስተካከለ መሆኑን አስታውቋል።

‎የግል ከፍተኛ ትምህርት፣ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት ማህበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ተፈራ ገበየሁ፤ ሚኒስቴሩ 'የሪሜዲያል ፕሮግራም ለመከታተል ተማሪዎች እንደተፈተኑት የትምህርት አይነት እና ብዛት ከ33 በመቶ እና ከዚያ በላይ ውጤት ማምጣት አለባቸው' የሚል ማስታወቂያ ማውጣቱ አስታውሰዋል።

‎ይሁንና፣ በተፈጥሮ እና ማኅበራዊ ሳይንስ ለወንዶች የተቀመጠው 216 የመግቢያ ነጥብ ወደ መቶኛ ሲቀየር 36 በመቶ እንደሚሆን ገልጸው፤ በመቶኛ እና በቁጥር መካከል ያለው ልዩነት ግርታን እንደፈጠረ ለአሐዱ ተናግረዋል።

‎አቶ ተፈራ፣ ጉዳዩን አስመልክቶ 36 በመቶ መሆኑን የሚያሳይ መረጃ ለተቋማት በኢ-ሜል መልዕክት መላኩን ገልጸዋል። "ነገር ግን ይህ መረጃ 'ይፋዊ አይደለም' መባሉ፤ የመረጃ መዛባት ስህተት እንዳያስከትል ስጋት ፈጥሮብናል" ሲሉም አክለዋል።

‎አሐዱ ጉዳዩን አስመልክቶ የትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማስተባበሪያ ዴስክ ኃላፊ ኢዮብ አየነው (ዶ/ር)ን ጠይቋል።

‎ኃላፊው በምላሻቸው፣ "ቁጥሮቹ ይፋ ሲደረጉ መስተካከል ያለባቸው እንዳሉ ተረድተናል" ያሉ ሲሆን፤ ሆኖም ግርታ እንዳይፈጠር በሚል ለተቋማቱ በዚህ ሳምንት የማስተካከያ ደብዳቤ እንደሚጻፍ ተናግረዋል።

‎አክለውም፤ "የተቀመጠው '33 ከመቶ' የሚለው ቁጥር 'አፈርማቲቭ አክሽን' ለሚሰጣቸው ክልሎች እና ዜጎች ብቻ የሚሰራ ውጤት ነው" ብለዋል፡፡

‎በመንግሥት ወጪያቸው የሚሸፈነው እና የግል ተቋማት ውስጥ ገብተው የሚማሩት ተማሪዎች ግን፤ 36 ከመቶ ወይም ወንድ 216 ሴት ደግሞ 204 የመቁረጫ ነጥቡን ያመጡ ተማሪዎች ብቻ እንደሆኑ አስረድተዋል።

‎ለታዳጊ ክልሎች እና አርብቶ አደር አካባቢዎች በሁለቱም የትምህርት ዘርፎች እና ለሁለቱም ጾታ 198 ነጥብ ተቀምጧል።

‎በተጨማሪም መስማት የተሳናቸው የተፈጥሮ እና የማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ መግቢያ 198 ሲሆን፤ ዓይነ ስውራን ደግሞ በሁለቱም የትምህርት ዘርፎች እና ጾታ 165 የማለፊያ ነጥብ ተወስኖላቸዋል። ይህ ቁጥርም በመቶኛ 33 ከመቶ ይሆናል ነው የተባለው።

‎#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ