ሰኔ 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሩሲያ የትራንስፖርት ሚኒስትር ሮማን ስታሮቮይት በፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከስልጣናቸው ከተሰናበቱ ከሰዓታት በኋላ ሞተው ተገኝተዋል ሲሉ የሀገሪቱ ባለስልጣናት አስታውቀዋል፡፡
ሮማን ስታሮቮይት ቀደም ሲል የደቡባዊ ሩሲያ ኩርስክ ክልል ገዥ ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩ ሲሆን፤ በማስከተልም እ.ኤ.አ ግንቦት 2024 ላይ የሩሲያ የትራንስፖርት ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል፡፡ ሆኖም ዛሬ ማለዳ ላይ ስታሮቮይት ከሚኒስቴርነት ኃላፊነታቸው በፑቲን ተሰናብተዋል።

ከሥራ መባረራቸውን የሚያበስረው መግለጫ በክሬምሊን ይፋዊ ድረ-ገጽ ላይ የወጣ ሲሆን፤ በመግለጫውም ምክትላቸው አንድሬ ኒኪቲን ተጠባባቂ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸው ተመላክቷል፡፡
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ ከስታሮቮይት መባረር በስተጀርባ ያለውን ምክንያት "በእምነት ማጉደል ምክንያት ነው" ያሉ ሲሆን፤ ነገር ግን ምንም ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡
የሩሲያ መርማሪ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ የስታሮቮይት አስከሬን በሞስኮ አቅራቢያ በሚገኘው ኦዲንትሶቮ በማሌቪች ፓርክ አቅራቢያ በመኪና ውስጥ መገኘቱን ገልጿል።
በጥይት ተመትተው መገኘታቸውን ያስታወቀው መግለጫው፤ የሞታቸው ሁኔታ እየተጣራ ቢሆንም "ዋናው ክስተት ግን ራስን ማጥፋት ነው" ብሏል።
ሚኒስትሩ ከዚህ ቀደም ከ2022 እስከ 2024 የደቡባዊ ሩሲያ ኩርስክ ክልል ገዥ በነበሩበት ወቅት፤ "በክልሉ ውስጥ ለመከላከያ ግንባታ የሚሆን ገንዘብ ዘርፈዋል" በሚል በእሳቸው ላይ ምርመራ ሊጀመርባቸው መሆኑን አርቲ ዘግቦ ነበር።
ስታሮቮይት በሚሊዮን ሩብል የስርቆት ክስ ተመስርቶባቸው በዛሬው ዕለት በሕግ ቁጥጥር ሥር ውለው ለምርመራ ሊቀርቡ እንደነበርም ተመላክቷል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ