ሰኔ 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአማራ ክልል እየታየ ያለው ነባራዊ ሁኔታ በየጊዜው መልኩን እየቀያየረ ቢሆንም፤ ሕዝብ በጫካ ያሉ ልጆቹን መክሮ ወደ ንግግር እንዲመጡ ያደርጋል ብሎ ተስፋ እንደሚያደርግ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታውቋል።
"በክልሉ አሁንም እየታዩ ያሉ ግጭቶች ቢኖሩም በጫካ ያሉት ወጣቶች ከአማራ ሕዝብ አብራክ የወጡ ስለሆኑ ሕዝቡ ጥያቄያቻቸውን ይዘው ወደ ንግግርና ውይይት እንዲመጡ ግፊት ያደርጋል ብየ አምናለሁ" ሲሉ ለአሐዱ የተናገሩት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶ/ር ዮናስ አዳዬ ናቸው።

"የወጣቶቹ ጥያቄ ተገቢ ነው ብለን እናምናለን" ያሉት ኮሚሽነሩ፤ "ነገር ግን ጥያቄን በጠመንጃ ሳይሆን ማስመለስ የሚቻለው በንግግር ነው" ሲሉ አፅንኦት ሰጥተዋል።
ኮሚሽኑ በክልሉ የሚቀሳቀሱ ታጣቂዎች በሚፈልጉት ቦታ ጥያቄያቸውን ለመቀበል ቁርጠኛ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ዮናስ፤ "ሆኖም ይህንን ማድረግ የሚቻለው ከእነሱ አወንታዊ የሆነ ትብብር ሲመጣ ነው" ብለዋል።
በክልሉ ከዚህ በፊት ጥሩ የሆነ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት መደረጉን ያስታወሱም ሲሆን፤ "ሆኖም ሙሉ ለሙሉ በክልሉ የሚቀሳቀሱ ተዋናዮችን አካተናል ብለን አናምንም" ሲሉ ተናግረዋል።
በዚህም ኮሚሽኑ የክልሉን ሕዝብ በመተማመን የአጀንዳ ማሰባሰብ መረሃ ግብሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
"የአማራ ሕዝብ ለሃገራዊ ሁለንተናዊ ሰላምና እድገት ከፍተኛ ሚና ሲጫወት የኖረ ሕዝብ ነው" ያሉት ዶ/ር አዳዬ፤ "አሁንም የገጠመውን አለመረጋጋት ቁጭ ብሎ በመምከር ችግሮችን ይፈታል ብለን እናምናለን" ብለዋል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በማረሚያ ቤት ውስጥ ሆነው የሕግ ሂደታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙ ዜጎችን በሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተሳታፊ የሚሆኑበት ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝ አስታውቋል።
በዚህም የሕግ ታራሚዎች በሀገራዊ የምክክር ኮምሽኑ ተሳታፊ የሚሆኑበትን ዕድል እንዲፈጠር ጥያቄዎች እንደሚቀርቡ አስታውቋል።

የኮሚሽኑ ቃል አቀባይና የዋና ኮሚሽነሩ ልዩ አማካሪ አቶ ጥበቡ ታደሠ፤ ጉዳያቸውን በሕግ እየተከታተሉ ያሉ እንጂ ውሳኔ ተላልፎባቸው በማረሚያ ውስጥ የሚገኙት ተሳታፊ እንደማይሆኑ ተናግረዋል፡፡
በዚህ ረገድ በሀገራዊ ምክክሩ ተሳትፎ ማድረጋቸው የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ እና በጎ ሚና እንደሚኖረው አንስተው፤ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡
"ምክክሮች እስካሁን ባለው ሁኔታ የኢትዮጵያ ዜጎች አጀንዳቸውን ተሰብስበው፣ ተሳትፎ አጀንዳዎች የሚቀረጹበት፣ በሂደቱም በሀገራቸው እጣፈንታ ላይ ተሳትፈውበት ውጤት ለማምጣት እየተሰራ ያለበት ጉዳይ ነው" ሲሉም አሳስበዋል።
አክለውም የሚካሄዱ ምክክሮች ድርድር ሳይሆኑ አንዱ አካል አሸናፊ ሌላው አካል ተሸናፊ ሆኖ የሚወጣበት መድረክ እንዳልሆነ ጠቁመው፤ "ምክክር ሁሉም አሸናፊ የሚሆኑበት መግባባት ላይ የሚደረስበት ነው" ብለዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ