ሰኔ 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራ ፍትሕ (ኢዜማ) ከሰኔ 28 እስከ 29 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ሲያካሂድ የነበረውን ሁለተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ፤ ፓርቲውን ለመጪው ሦስት ዓመታት የሚመሩ አመራሮችን በመምረጥ አጠናቋል።
ኢዜማ "በሃሳብ እንፎካከራለን፤ ስለ ሀገር እንተባበራለን!" በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ሲያካሂድ በነበረው ሁለተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔው ላይ፤ ከመላ ሀገሪቱ ከሚገኙ የፓርቲው የምርጫ ክልሎች የተወከሉ ከ600 በላይ አባላት መሳተፋቸውን ለአሐዱ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡
በየሦስት ዓመቱ የሚከናወነው ይህ የኢዜማ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ የፓርቲው ከፍተኛ የሥልጣን እርከን ሲሆን፤ ከተለያዩ የሥራ ክፍሎች የቀረቡለትን የፓርቲውን የሦስት ዓመት የሥራ ክንውን፣ የሂሳብ እና የኦዲት ሪፖርት እንዲሁም የደንብ ማሻሻያ እና ፓርቲውን ለመጪው ሦስት ዓመት የሚመሩ አመራሮችን በመምረጥ ጉባዔውን በስኬት ማጠናቀቁን ገልጿል፡፡

በዚህም መሠረት ሰኔ 28 ቀን 2017 ዓ.ም በተከናወነው የመጀመሪያ ቀን መርኃ ግብር፤ የፓርቲው ኦዲት እና ኢንስፔክሽን እንደዚሁም የሕገ ደንብ ተርጓሚ እና ሥነ-ምግባር ኮሚቴዎች የሥራ ሪፖርታቸውን አቅርበው በጠቅላላ ጉባዔው ጸድቋል፡፡
በመቀጠልም የፓርቲው የድርጅት ክንፍ ሪፖርት በፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ ማዕረጉ ግርማ ቀርቦ ሰፊ ውይይት እና ማስተካከያ ከተደረገበት በኋላ ጸድቋል፡፡
በተመሳሳይ የፓርቲው ምክትል መሪ አርክቴክት ዮሃንስ መኮንን የፓርቲውን የመሪ ክንፍ የሥራ ሪፖርት አቅርበው፤ በአባላት በርካታ ጥያቄዎች እና ሰፊ ውይይት ከተደረገ በኋላ ሪፖርቱ ከማሻሻያ ጋር ጸድቋል፡፡
የፓርቲው አንደኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ላለፉት በርካታ ወራት የፓርቲውን ደንብ ለማሻሻል በሕግ ባለሙያዎች የተዋቀረው ቡድን ያቀረባቸው የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያ ሃሳብ ላይ ሰፊ ውይይት እና ገለፃ ከተደረገ በኋላ በአባላት መጽደቁ ተገልጿል።
የተደረገው ማሻሻያ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዲቀርብ መወሰኑንም ፓርቲው በመግለጫው አመላክቷል፡፡

በተጨማሪም ትናንት እሑድ ሰኔ 29 ቀን 2017 ዓ.ም በተከናወነው በሁለተኛው ቀን መርኃ ግብር የፓርቲው መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ለጉባኤተኞች ባስተላለፉት መልዕክት፤ ፓርቲው ከውስጥም ሆነ ከውጪ ሲሰነዘርበት የቆዩትን ተግዳሮቶች በመቋቋም የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ባህል እና የዜግነት ፖለቲካ በጽኑ መሰረት ላይ እንዲቆም ጉዞውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

አክለውም፤ ፓርቲው በ2018 ዓ.ም ለሚደረገው ሀገራዊ ምርጫ ከወዲሁ ዝግጅቱን መጀመር እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
በመጨረሻም በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት በየሦስት ዓመቱ የሚከናወነውን የፓርቲውን የድርጅት ክንፍ የአመራር ፣ የኦዲት እና ኢንስፔክሽን እንዲሁም ሕገ ደንብ ተርጓሚ እና ሥነምግባር ኮሚቴ አባላት ምርጫ አከናውኗል፡፡
በዚህም መሠረት፦
1. ዶ/ር ሙሉዓለም ተገኘወርቅ የፓርቲው ሊቀመንበር
2. አቶ ማዕረጉ ግርማ የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር
3. አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ የፓርቲው ዋና ፀሐፊ
4. ወ/ሮ አሰፉ ተረፈ የፓርቲው ፋይናንስ/ትሬዢረር በመሆን ተመርጠዋል፡፡
በተመሳሳይም ፓርቲውን ለመጪው ለሦስት ዓመት የሚያገለግሉ አምስት አምስት አባላት ያሉት የኦዲት እና ኢንስፔክሽን እንዲሁም ሕገ ደንብ ተርጓሚ እና ሥነ-ምግባር ኮሚቴ አባላትም ተመርጠዋል፡፡
በመጨረሻም ፓርቲውን ለቀጣይ ሦስት ዓመት የሚመሩ አመራሮች ቃለመሃላ በማድረግ ጠቅላላ ጉባዔው ማጠናቀቁን በመግለጫው አስታውቋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ