ሕዳር 25/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ከ8 በላይ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ 400 ተሳታፊዎች የሚታደሙበት የአፍሪካ የመጀመሪያው የኢነርጂ ውጤታማነት ጉባኤ በአዲስ አበባ ሊካሄድ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በአፍሪካ ሕብረት የተዘጋጀው ይህ ጉባኤ ታሕሣሥ 2 እና 3 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በሚገኘው የሕብረቱ ዋና መሥሪያ ቤት እንደሚካሄድ ነው የተነገረው።
ጉባኤው በአፍሪካ እየተጋረጠ ያለውን የኃይል አቅርቦት ክፍተት በመሙላት ረገድ ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው ተጠቁሟል።
የአፍሪካ ሕብረት መሠረተ ልማት እና ኢነርጂ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌራቶ ማዳቦሄ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ የጉባኤው ዋነኛ ዓላማ ለሁሉም አፍሪካውያን ተመጣጣኝ፣ አስተማማኝ፣ ዘላቂ እና ዘመናዊ ኃይል ተደራሽነትን ማረጋገጥ ነው።

ኮሚሽነሯ የኢነርጂ ውጤታማነት አስፈላጊነትን ሲያብራሩ፤ ፈጣን የሕዝብ ቁጥር መጨመር እና የከተሞች መስፋፋት አፍሪካ የኢነርጂ ክፍተት እንዲጋረጥባት አድርጓል ብለዋል። ይህ ክፍተት ኢኮኖሚያዊ ፍላጎትን የሚያዳክም እና ያለውን ኢፍትሐዊነት የሚያባብስ ስለመሆኑም አንስተዋል።
ኮሚሽነር ሌራቶ ማዳቦሄ እንዳሉት፤ የኢነርጂ ውጤታማነት ንፁህ፣ ዋጋው ተመጣጣኝ እና ፈጣን የሆነ ኃይልን በማቅረብ ድህነትን ለመቀነስና ዘመናዊ የኢነርጂ አገልግሎቶችን በቅናሽ ዋጋ ተደራሽ ለማድረግ ይረዳል።
በዚህም አህጉሪቱ ኃይልን ቆጥባ በመጠቀም በፈጣን የከተሞች መስፋፋት እና በኢንዱስትሪ ልማት ላይ የምትገኘውን አፍሪካ መደገፍ የሚችል ሥርዓት መዘርጋት ትችላለች።
ኢነርጂን በውጤታማነት መጠቀም ለ600 ሚሊዮን ሕዝብ የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ለማዳረስ እና ወደ 1 ቢሊዮን የሚጠጋውን ዜጋ ንፁህ የምግብ አዘገጃጀት መፍትሔ ማግኘት የሚያስችል አቅም ይፈጥራል ተብሏል።
የኢነርጂ ውጤታማነት ለኢኮኖሚ ውጤታማነትና ወጪ ቆጣቢ በመሆኑ አላስፈላጊ የኃይል ፍላጎትን በመቀነስ በቢሊዮን የሚቆጠር የመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንትን ማዳን የሚያስችል መሆኑንም ኮሚሽነሯ ገልጸዋል።
በዚህ የአፍሪካ ኢነርጂ ውጤታማነት ጉባኤ ወደ 400 የሚጠጉ የከፍተኛ ደረጃ ተሳታፊዎች የሚገኙበት ሲሆን፤ ከስምንት በላይ አባል ሀገራት የኢነርጂ ላይ የሚሠሩ ኃላፊዎች፣ የቀጠናዊ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ክፍሎች ከፍተኛ ተወካዮች እና የብሔራዊና ቀጠናዊ ኢነርጂ ተቆጣጣሪ አካላት ይገኛሉ።
የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር ባህሩ ኦልጅራ እንዳሉት፤ ጉባኤው በአፍሪካ ሕብረት እና በኢትዮጵያ የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን በጋራ እየተስተናገደ ያለ የመጀመሪያው የአፍሪካ ኢነርጂ ውጤታማነት ጉባኤ ነው።
መርሐ ግብሩን በማዘጋጀት ሂደት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲሁም የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር መሳተፋቸውን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የ10 ዓመታት ስትራቴጂካዊ ልማት አንዱ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ዕድገት ማረጋገጥ በመሆኑ፤ ይህ ጉባኤ ኢትዮጵያ የኢነርጂ ውጤታማነትን ለማሳካት ለምታደርገው ጥረት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት በሀገር አቀፍ ደረጃ ኃይል ቆጣቢነትን በኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ዘርፎች ለማረጋገጥ ስትራቴጂዎች እየተተገበሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ኮንፈረንሱ እ.ኤ.አ. በ2024 በአዘርባጃን ባኩ በተካሄደው 29ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 29) ይፋ በተደረገው የአፍሪካ ኢነርጂ ውጤታማነት ጥምረት ማዕቀፍ ሥር የሚካሄድ ነው። የጉባዔው መሪ ሐሳብም "የአፍሪካ የኢነርጂ ውጤታማነት አጀንዳን በስትራቴጂያዊ አጋርነት እውን ማድረግ" የሚል ነው።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ