ሕዳር 18/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የአፍሪካ ሕብረት፣ የምዕራብ አፍሪካ ህብረት (ECOWAS) እና የሀገር ሽማግሌዎች ፎረም ታዛቢ ተልዕኮዎች በጊኒ-ቢሳው የተፈፀመውን ወታደራዊ መፈንቀለ መንግሥት አወግዘዋል።

የምርጫ ታዛቢ መሪዎቹ፤ የጊኒ-ቢሳው ወታደራዊ መኮንኖች የፈፀሙት ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት፤ "የዲሞክራሲያዊ ሂደትን ለማደናቀፍ የተደረገ ግልፅ ሙከራ ነው" ሲሉ አስታውቀዋል።

መሪዎቹ ይህን መግለጫ የሰጡት፤ ባለፈው እሁድ ዕለት የተካሄደውን የፕሬዚዳንት ምርጫ የሀገሪቱ ምርጫ ቦርድ አሸናፊውን ሳያሳውቅ ገና ከወዲሁ፤ ወታደራዊ መኮንኖቹ የወቅቱ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንትን ጨምሮ ተፎካካሪ የምርጫ ተወዳዳሪዎቹን ከየ ቢሮቸው በማባረር ጠቅላይ ስልጣኑን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ ነው።

በዚህም ራሳቸውን "የብሔራዊ ደኅንነት እና ሕዝባዊ ስርዓትን መልሶ ማቋቋም ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ" በማለት የገለጹ የወታደራዊ መኮንኖች ቡድን፤ በመንግሥት ቴሌቪዥን ቀርበው ትላንት እኩለ ለሊት ላይ በሰጡት መግለጫ የመንግሥትን ሙሉ ስልጣን መቆጣጠራቸውን አስታውቀዋል።

ወታደሮቹ ሁሉንም የብዙሃን የመገናኛ አውታር እንቅስቃሴዎች መገደባቸውንም አናዶሎ ዘግቧል።

እንዲሁም የተጀመረውን የምርጫ ሂደት ተቋርጧል፣ ድንበሮችን ሁሉ ዘግተዋል በሀገሪቱ ሰዓት እላፊ ጥለዋል።

የምርጫ ታዛቢ ልዑካን መሪዎች የአፍሪካ ህብረት እና ኢኮዋስ ሕገ-መንግሥታዊ ስርዓቱን ወደነበረበት ለመመለስ አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድም ጠይቀዋል።

"የዴሞክራሲ ሂደቱን ለማደናቀፍ የሚደረገውን አይን ያወጣ ሙከራ አናወግዛለን" ያሉት መሪዎቹ፤ እስካሁን የተገኙትን ድሎች መደናቀፋቸውንም አሳዝዝኖናል ብለዋል።

የምርጫውን ሂደት ሲመሩ የነበሩትን ጨምሮ ባለስልጣናት በመታሰራቸውም ስጋታቸውን አንስተዋል።

"ከዚህ ጋር በተያያዘ የታጠቁ ኃይሎች የሀገሪቱ የምርጫ ሂደት ወደ መደምደሚያው እንዲደርስ ለማስቻል የታሰሩ ባለስልጣናትን በአስቸኳይ እንዲፈታ እናሳስባለን" ሲሉ ታዛቢዎቹ አክለዋል።

የታዛቢ ልዑካኑ የጊኒ-ቢሳው ሕዝብ ለጠንካራ ሕዝባዊ ተሳትፎ አመስግነዋል። የድምፅ አሰጣጡ ሂደት በሥርዓት እና በሰላማዊ መንገድ የተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሆኖም መፈንቅለ መንግሥቱ የተፈፀመው፤ የምርጫ ኮሚሽኑ የምርጫው አሸናፊ ማን እንደሆነ የመጨረሻ ውጤቱን በዛሬው ዕለት ተብሎ ሲጠበቅ በነበረበት ወቅት ነው።

በደረጄ መንግስቱ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ