መስከረም 20/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ‎ለአንድ ሳምንት ያህል በሕዝባዊ እምቢተኝነት ተቀስቅሶበት የቆየው የማዳጋስካር መንግሥት በመጨረሻም አስተዳደራዊ መዋቅሩ መፍረሱ ተነግሯል።

የማዳጋስካር ፕሬዝዳንት አንድሪ ራጆሊና ለአንድ ሳምንት ያህል የገጠማቸውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ለማስቆም የፀጥታ አካላት አሰማርተው ስልጣናቸውን ለማዳን ሲሉ ጥረት ቢያደርጉም፤ ይህ ጥረታቸው ሳይሳካ ቀርቶ የሀገሪቱ ካቢኔ እንዲበተን አድርገዋል፡፡

Post image

"ጄን ዚ" በመባል የሚጠሩት በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣት የአዲሱ ትውልድ አባላት ያደረጉትን ተቃውሞ ተከትሎም፤ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት የሕዝቡን ጥያቄ በመቀበል አሁን ያለውን ካቢኔ አፍርሰው እንደ አዲስ ለማዋቀር ቃል ገብተዋል።

በዚህም የተነሳ አዲስ ካቢኔ በቀጣይ ሦስት ቀናት ውስጥ እንደሚቋቋም ጠቁመዋል።

ይህ ሁከትና ብጥብጥ ባስነሳው ተቃውሞ ምክንያት ቢያንስ 22 ሰዎች ለሕልፈት ሲዳረጉ፣ ከ100 በላይ የሚሆኑት ጉዳት እንደደረሰባቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ነገር ግን የማዳጋስካር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የድርጅቱን ቁጥራዊ መረጃ ውድቅ ያደረገ ሲሆን፤ "በአሉባልታ ወይም የተሳሳተ መረጃ ላይ የተመሰረተ ነው" ብሎታል።

"ጄን ዚ" የተሰኙት የአዲሱ ትውልድ አባላት በተቃውሞ ሰልፍ የሀገሪቱን ከተሞች ማጥለቅለቅ የጀመሩት ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ዕለት ነበር።

በትናንትናው ዕለትም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች ወደ አደባባዮች በመውጣት በመንግሥት ላይ ተቃውሟቸውን ያሰሙ ሲሆን፤ ፖሊስም የተሰበሰቡ ሰዎችን ለመበተን የፕላስቲክ ጥይት እና አስለቃሽ ጭስ ተጠቅሟል፡፡

Post image

ይህንንም ተቃውሞ ተከትሎ፤ የማዳጋስካር ፕሬዝዳንት አንድሪ ራጆሊና በመዲናዋ ከትናንት ጀምሮ የሰዓት እላፊ ገደብ እንዲጣል ትዕዛዝ ሰጥተው የነበረ ቢሆንም፤ ተቃውሞው እየጨመረ በመምጣቱ ምክንያት በሀገራቸው አስተዳደር ላይ ለውጦችን ለማድረግ ቃል ገብተዋል።

ፕሬዝዳንት ራጆሊና በ2023 ለሦስተኛ ጊዜ ከተመረጡ ወዲህ ያጋጠማቸው ትልቁ ተቃውሞም ስለመሆኑ ተነግሯል።

በደቡባዊ አፍሪቃዊቷ ሀገር ርዕሰ መዲና አንታናናሪቮ በወጣቶች መራሹ 'ጄን ዚ' ንቅናቄ የተካሄደው ይህ ተቃውሞ፤ በሀገሪቱ ስምንት ከተሞች ላይ ተስፋፍቶ ቆይቷል።

በሀገሪቱ ለዓመታት በዘለቀው የሙስና እና የመልካም አስተዳደር እጦት ተባብሷል ሲሉ የከሰሱት ተቃዋሚዎች፤ አስተማማኝ የመብራት እና የንፁህ መጠጥ ውሃ መንግሥት እንዲያቀርብ ጠይቀዋል።

Post image

መንግሥት ተቃውሞውን ለማገድ የፀጥታ አካላት አሰማርቶ የነበረ ቢሆንም፤ ተቃዋሚዎቹ ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ወደ ግጭት ውስጥ ገብተው በሰው ላይ እና በንብረት ላይ ከፍተኛ የተባለ ውድመት ደርሷል፡፡

ተቃዋሚዎች የመኪና ጣቢያዎችን አቃጥለዋል፣ ሱቆችን ዘርፈዋል፣ የሁለት የፓርላማ አባላት መኖሪያ ቤት ላይም ጥቃት ማድረሳቸውም ታውቋል፡፡

የፖሊስ እና ወታደራዊ ጥምር የደህንነት አካልን የሚመሩት አንጄሎ ራቬሎናሪቮ የግል ብዙኃን መገናኛ በሆነው ሪል ቲሌቭዥን በሰጡት መግለጫ፤ "ግለሰቦች ተቃውሞውን የሌሎችን ንብረት ለማውደም ተጠቅመውበታል ሲሉ" ክስ አቅርበዋል።

Post image

ፕሬዝዳንት አንድሪ ራጆሊና ብጥብጡን "አሳዛኝ እና ሕመም" ሲሉ አውግዘውታል፡፡ አክለውም "አጥፊ አስተሳሰብ” ማዳጋስካርን ማሳደግ እንደማይችል አስታውቀዋል።

የአፍሪካ ሕብረት በህንድ ውቅያኖስ ደሴት ላይ የተከሰቱትን አሳሳቢ ክስተቶች እየተከታተለ መሆኑን ገልጾ፤ ቀውሱን ለመፍታት ከመንግሥት እና ከክልሉ የደቡብ አፍሪካ የልማት ማህበረሰብ (ሳዲክ) ጋር በጋራ ለመስራት ቃል ገብቷል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ