መስከረም 20/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ ዕድሜያቸው 60 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑ 6 ነጥብ 8 ሚሊዮን 700 ሺሕ ብቻ አረጋውያን እንደገሚገኙ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ሚኒስቴሩ ይህን የገለጸው ከኢትዮጵያ አረጋዊያንና ጡረተኞች ብሔራዊ ማኅበር ጋር በመተባበር ነገ መስከረም 21 ቀን 2018 ዓ.ም የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የአረጋዊያን ቀን አስመልክቶ በትናንትናዉ ዕለት በተሰጠው መግለጫ ላይ ነው።
ከነዚህም ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ አረጋዊያን ለፖለቲካዊ፣ ለኢኮኖሚያዊና ለማኅበራዊ ችግሮች ተጋላጭ መሆናቸው የተነገረ ሲሆን፤ ከሕዝብ ብዛት አንፃር ቁጥራቸው ዝቅተኛ እንደሆነ ተገልጿል።
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የማኅበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ ወ/ሮ ሁሪያ አሊ፤ በሀገሪቱ ዕድሜያቸው 60 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑ 6 ነጥብ 8 ሚሊዮን 700 ሺሕ አረጋዊያን ብቻ እንደሚገኙ የገለጹ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ መሆናቸውን ተናረዋል።
በሀገሪቱ ውስጥ ለተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ችግሮች የተጋለጡ አረጋዊያን ቁጥራቸው ቀላል የሚባል እንዳልሆነም አመላክተዋል።
መጠለያ የሌላቸውና በቂ ምግብ የማያገኙ፣ ለተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮችም የተጋለጡ በርካታ መሆናቸውን ሚኒስትር ደኤታዋ ለአሐዱ ተናግረዋል።
የሀገር ባለውለታ ለሆኑት አረጋውያን ተገቢውን ክብርና ፍቅር መስጠት፣ መብታቸውንና ጥቅማቸውን ማስከበር ብሎም ሁሉን አቀፍ ድጋፍና ክብካቤ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
አረጋዊያን ባሳለፉት ረጅም የእድሜ ዘመናቸው ዕውቀታቸውንና ጉልበታቸውን ለልማት ያዋሉ፤ የሕዝብና የሀገር ባለውለታ መሆናቸውን ገልጸዋል።
አቅማቸው በደከመ ጊዜ በተለይም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ የሀገር ባለውለታ አረጋውያንን መደገፍና መንከባከብ ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ኃላፊነት መሆኑን አስገንዝበዋል።
አረጋውያን እውቀታቸውንና ልምዳቸውን ማስተላለፍ የሚችሉበትን ሁኔታ በማመቻቸት የትውልድ ቅብብሎሹ እንዲቀጥል ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።
አረጋውያን ከእድሜ ጋር ተያይዘው ልዩ ልዩ ፈተናዎች የሚገጥሟቸው ችግሮች ደረጃ በደረጃ ለመቅረፍና ፍላጎቶቻቸውን በሚፈለገው መልኩ ለማሟላት መንግሥት እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን ተናግረዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የአረጋውያንን ጉዳይ የሚከታተልና የሚያስተባብር ክፍል በመሪ ሥራ አስፈጻሚ ደረጃ በማደራጀት መዋቅሩን እስከታች ለመዘርጋት ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን የአሰራር ማዕቀፎችን የመቅረጽና የአስፈጻሚ አካላትን አቅም የማጎልበት ስራ በትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በቀጣይም ለአረጋውያን የተሻለ ተጠቃሚነት በተለያዩ አካላት ለሚያደረጉ ጥረቶች ስኬታማነት አስፈላጊውን እገዛና ድጋፍ ያደርጋል ሲሉ ተናግረዋል።
አረጋውያን በመጦሪያ ዘመናቸው የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች ለመፍታትና ለመደገፍ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።
የአረጋውያን እና አቅመ ደካሞችን ቤት ለማደስና አዲስ ለመገንባት፣ በማዕከል ደረጃ ድጋፍና ክብካቤ እንዲያኙ ለማድረግ እና ተሳትፏቸውን ለማጠናከር የተጀመሩ ሥራዎች ቀጣይነት እንደሚኖራቸው አሳስበዋል።
አረጋዊያን መብታቸው ተክብሮ ከልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ፤ ሁሉም ዕድሜው ሲገፋ የሚደርስበትን "የነገ ቤቱን ዛሬ መስራት አለበት" ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ለችግር የተዳረጉ አረጋዊያንን መደገፍና የሚመለከተው አካልም ተገቢውን ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው አክለዋል።
የኢትዮጵያ አረጋውያንና ጡረተኞች ብሔራዊ ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ሀይሌ በበኩላቸው፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ2 ነጥብ 1 በላይ አባላትን ያቀፉ 1 ሺሕ 326 የአረጋውያን ማህበራት እንዳሉ ገልጸዋል፡፡
እነዚህም ማህበራት የአረጋውያንን ችግሮች ለመፍታት በጋራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ዓለም አቀፍ የአረጋዊያን ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ35ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለ34ኛ ጊዜ "ለአረጋውያን ደህንነት እና መብቶች መጠበቅ ሁለንተናዊ ኃላፊነት እንወጣ "በሚል መሪ ሃሳብ በነገው ዕለት መስከረም 21 ቀን 2018 ዓ.ም ይከበራል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
#አሐዱ #ahadu #AhaduTV#ahaduRadio#Ethiopia
በኢትዮጵያ በአጠቃላይ 6 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብቻ አረጋውያን እንደሚገኙ ተነገረ
በሀገር አቀፍ ደረጃ 1 ሺሕ 326 የአረጋውያን ማህበራት መኖራቸው ተገልጿል
