መስከረም 14/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በማዕከላዊ ጎንደር ምሥራቅ በለሳ ወረዳ ቤተ ክህነት ስር የሚገኘው የሙት አንሣ ማር ቅዱስ ሚካኤል አንድነት ገዳም መነኮሳትን ለመደገፍ በማህበራዊ ሚዲያ በተሠራ የገቢ ማሰባሰብ ሥራ፤ 30 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ መሰብሰቡ ተገልጿል፡፡

በተለያዩ ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት ችግር ላይ ወድቀው የሚገኙትን ገዳማት እና መነኮሳት ለመደገፍ በማህበራዊ ሚዲያ እንዲሁም በቴሌቪዥን እና ራዲዮ ማስታወቂያዎችን በቀረበው ጥሪ መሠረት፤ እስካሁን 29 ሚሊዮን 750 ሺሕ ብር የገንዘብ ድጋፍ መሰብሰብ መቻሉን የገዳሙ አባቶች በዛሬው ዕለት በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

በተጨማሪም 6 ሚሊዮን 208 ሺሕ 810 ብር የሚገመት የአይነት ድጋፍ መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል።

በዚህም ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ብፁዕ አቡነ መቃሪዮስ የምዕራብ ካናዳ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ፣ መጋቢ ሐዲስ ፍሰሐ በጠቅላይ ቤተክህነት የገዳማትና አድባራት መምሪያ ክፍል ዋና ፀሐፊ፣ መልአከ ገነት ቄስ አደራጀው ከፍያለው የማዕከላዊ ጎንደር ሀገረ ስብከት በምስራቅ በለሳ ወረዳ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ አባ ብርሃነ ሰላም ሙሃባው የገዳሙ ቄሰ ገበዝ ተገኝተዋል።

Post image

የሙት አንሣ ማር ቅዱስ ሚካኤል አንድነት ገዳም ቄስ ገበዝ አባአምላከ ብረሀን ሰላም ለአሐዱ እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ወቅት በገዳሙ ውስጥ 150 ገዳማዊን ይገኛሉ፡፡

በሙት አንሳ ማር ቅዱስ ሚካኤል አንድነት ገዳም የተጀመረው ፕሮጀክት 18 ወራትን ያስቆጠረ ሲሆን፤ በእነዚህ ጊዜያት በመጀመሪያ ምዕራፍ የፕሮጀክቱ 45 በመቶ በላይ ማሳካት መቻሉ ገልጸዋል።

ለገዳማውያኑ ለእንቅስቃሴ የማይመች እና አዳጋች የነበረው መንገድ 179 ሜትር ተራራ ተቦርቡሮ በአርማታ ደረጃ መሰራቱንም የገለጹ ሲሆን፤ ለገዳማዊያን እንቅስቃሴ ምቹ እንዲሆን ተደርጓል ብለዋል።

አካባቢው በተደጋጋሚ በድርቅ የሚጠቃ በመሆኑ በተሰራው የመልካ ምድር ሥራ የሚገጥመውን የምግብ ዋስትና በተወሰነ መልኩ መፈታቱን ገልጸዋል።

ከሕዝበ ክርስቲያኑ በተገኘው ገቢ በገዳሙ ትምህርት ቤት፣ የማምረቻ ሼድ፣ የሴት ገዳማዊን መኖሪያ ቤት እና የኤሌትሪክ አገልግሎት በአካባቢው ባለመኖሩ በሶላር የኤሌትሪክ አገልግሎት እንዲኖር መደረጉን ተናግረዋል።

በተጨማሪም፤ "የቤተ እግዚአብሔር ግንባታ ተከናውኖ ሙሉ ቁሳቁስ ተሟልቶ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል" ብለዋል።

በገዳሙ ለሚሰራው ሥራ ችግር የሆነው በአካባቢው ያጋጠመው የሰላም ችግር እና የግንባታ እቃዎች መናር ስለመሆኑም አስታውቀዋል።

ገዳሙ የገቢ ማሰባሰቢያ ሥራውን በጎንደር እና ባህርዳር ከተሞች አጠናክሮ እንደሚቀጥልም የገለጹት ቄስ ጎበዝ፤ የተለያዩ ባዛሮችን በማዘጋጀት በገዳሙ ላይ የሚመረቱ ምርቶችን ለምዕመኑ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

Post image


በአሁኑ ወቅትም ለአብነት ት/ቤት፣ ከቅድመ አንደኛ ደረጃ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትቤት፣ መካከለኛ ደረጃ ጤና ጣቢያ እና ሌሎች አስፈላጊ የልማት ሥራዎች የሚሰሩበት ሕንጻ ግንባታ የሚገነባበት፤ 30 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ በሀሙሲት ከተማ ላይ ከመንሥስት በሊዝ መረከቡን አስታውቀዋል፡፡

በገዳሙ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን ከፍጻሜ ለማድረስ እና ገዳማዊኑ ካሉባቸው ተደራራቢ ችግሮች እንዲወጡ ለማድረግና በቀጣይ ለሚሰሩትን የልማት ሥራዎች ለማከናወን 210 ሚሊዮን ብር የሚያስፈልግ መሆኑን አንስተው፤ ሕዝበ ክርስቲያኑ ድጋፍ የማድግ ሥራውን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።

ይህንንም ለማሳካት ጥቅምት 16 ቀን 2018 ዓ.ም ከቀኑ 5፡00 ጀምሮ በሚሊኒየም አዳራሽ "ገዳማዊ ልማት ለቤተክርስትያን ትሩፋት" በሚል መሪ ቃል ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት እና ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን በተገኙበት የገቢ ማሰባሰቢያ ጉባኤ መዘጋጁን አስታውቀዋል፡፡

በዚህም ጉባኤ ላይ ከ10 ሺሕ በላይ ሰዎች ይታደሙበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ በመግለጫው ተነግሯል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ