ጥቅምት 28/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮጵያ በሳማርካንድ፣ ኡዝበኪስታን እየተካሄደ በሚገኘው 43ኛው የዩኔስኮ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በዩኔስኮ የሥራ አስፈፃሚ ቦርድ አባል ሀገር ሆና ተመርጣለች።

በጠቅላላ ጉባኤው ማብቂያ ክፍት የሚሆኑትን የሥራ አስፈፃሚ ቦርድ አባላት መደብ የሚሞሉና እስከ 45ኛው የሥራ ዘመን መጨረሻ ድረስ የሚያገለግሉ አባል ሀገራትን ጉባኤው ዛሬ ጥቅም 28 ቀን 2018 ባካሄደው ስብሰባ መርጧል።

Post image

የሥራ አስፈፃሚ ቦርዱ ከጠቅላላ ጉባኤው እና ሴክሬታሪያት በተጨማሪ በዩኔስኮ ከሦስቱ መሠረታዊ አካላት አንዱ ሲሆን፤ በጠቅላላ ጉባኤው ይመረጣል።

በጠቅላላ ጉባኤው ሥልጣን ሥር የሚሰራው ይህ ቦርድ ለተቋሙ የሥራ መርሐ-ግብር እና በዋና ዳይሬክተር የቀረበለትን ተጓዳኝ የበጀት ግምት በመመርመር ከውሳኔዎቹ ጋር ለጠቅላላ ጉባኤ ያቀርባል።

ኢትዮጵያ በቦርድ አባልነት መመረጧ እንደ ሀገር ብሎም እንደ አህጉር የኢትዮጵያንና የመላው አፍሪካን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅና ከዩኔስኮ ዓላማና ተልዕኮ አንፃር በባለብዙ መድረኮች ድምጿን ለማሰማት መልካም አጋጣሚን እንደሚፈጥር በፈረንሳይ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታውቋል።

Post image

ቦርዱ እያንዳንዳቸው የአራት ዓመት የሥራ ዘመን ያላቸው 58 አባል ሀገራትን ያቀፈ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. እስከ 2029 በቦርድ አባልነቷ ከሌሎች ሀገራት ጋር በቅንጅትና በአብሮነት ለጋራ ውጤት የምትሰራ ይሆናል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ