መስከረም 12/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ‎የመስቀል ደመራ በዓል ሲከበር ከቤተ-ክርስቲያኒቱ ሰንደቅ ዓላማና ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ውጪ መያዝ የተፈቀዱ አለመሆናቸውን ‎የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ገልጸዋል።

የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የሸገርና የደቡብ ምዕራብ ሸዋ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የ2018 ዓ.ም መስቀል በዓል አከባበርና አጠቃላይ ዝግጅትን በተመለከተ ዛሬ ሰኞ መስከረም 12 ቀን 2018 መግለጫ ተሰጥተዋል።

‎ብፅዕነታቸው በመልዕክታቸው ከአደባባይ በዓላት መካከል አንዱ የሆነው የመስቀል ደመራ በዓልን ስናከብር፤ ከቤተክርስቲያን አስተምህሮ ውጪ የሆኑ አለባበሶችንና ልዩነትን የሚፈጥሩ አለባበሶችን ማስወገድ ይገባል ብለዋል።

‎የመስቀል በዓል ከሀገር አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ እውቅና ያለው መንፈሳዊ በዓል ነው ያሉ ሲሆን፤ በምናስተላልፋቸው ምልእክቶችም ሆነ በምንለብሳቸው ልብሶች ሰላምን ለዓለም ማወጅ አለብን ሲሉ ተናግረዋል።

Post image


‎"መስቀል እንደምልክት ለክርስቲያኖች የተሰጠው እግዚአብሔር በማመንና በመፍራት ስለምንመላለስ በመሆኑ፤ መስቀል በሁለንተናችን ሊገለጥ እንዳለበት እንዲሁም፤ የመስቀል በዓል የሰላም በዓል በመሆኑ የበዓሉ አከባበር ሰላምንና ፍቅርን የሚሰብክ ሊሆን ይገባል" ሲሉ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ገልጸዋል።

‎በበዓሉ ላይ ኢትዮጵያዊ ባህልን የጠበቀ የአለባበስ ሥርዓት መከተል እንደሚገባና ልዩነትን የሚሰብክ አለባበስም ሆነ ምልክት መጠቀም እንደማይገባ አሳስበዋል፡፡
‎በተጨማሪም በበዓለ መስቀሉ ዕለት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ እና የቤተ ክርስቲቱን ዓርማ ብቻ መጠቀም ይገባል ብለዋል ብፁዕነታቸው።

Post image

‎ክብረ በዓሉን በሰላማዊ መንገድ ለማክበር ኮሚቴ ተዋቅሮ የረጅም ጊዜ ዝግጅት መደረጉን እና በዓሉ በሠላም ተጀምሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ስለመሆኑም ተገልጿል።

‎"የመስቀል በዓልን በመስቀሉ የተደረገልንን ፍቅር በማሰብ የሚከበር ነው" ያሉት ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ፤ ሕዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን ሲያከብር እንደሁልጊዜው መንፈሳዊነቱን ጠብቆው እንዲያከር መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ