መስከረም 12/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የ2018 የመስቀል ደመራ በዓል በሕብረተሰቡ ላይ ጉዳት የሚያደርስ ምንም አይነት አደጋ ሳይከሰት እንዲከበር ለማድረግ፤ በቂ ዝግጅት ማድረጉን የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ለአሐዱ አስታውቋል።

የመስቀል ደመራ በዓል ዝግጅት ከአዲስ ዓመት ጋር በአንድ ላይ እቅድ ተካትቶ ሲሰራበት መቆየቱን የገለጹት፤ የኮሚሽኑ የአደጋ ስጋት ጥናትና ትግበራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደሲሳ ጦና ናቸው።

በዓሉ የአደባባይ በዓል ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እና በርካታ ሕዝብ የሚገኝበት በመሆኑ የእሳት አደጋን ጨምሮ ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች ሊከሰቱ የሚችሉበት እድል እንዳለ አንስተዋል።

በተጨማሪም የትራፊክ አደጋ እና በቤት ውስጥ በሚሰራ ሥራ የከሰል ጭስ አደጋ ሊያጋጥም ይችላል ብለዋል።

በመሆኑም የመስቀል ደመራ በዓሉ ያለምንም አደጋ እንዲከበር ለማድረግ ሰፊ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ገልጸዋል።

Post image

ከመስቀል ደመራ በተጨማሪም ለኢሬቻ በዓል አከባበርም እንዲሁ፤ ተመሳሳይ ቅድመ ዝግጅት መሰራቱን ተናግረዋል።

ዳይሬክተሩ አክለውም፤ ማንኛውም ድንገተኛ አደጋ እንዳይከሰት ማህበረሰቡ የሚሰጠውን ምክረ ሀሳብ በመቀበል ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸው፤ አደጋ ከተከሰተ ግን ወዲያውኑ ማሳወቅ ይገባል ብለዋል።

ማህበረሰቡ ድንገተኛ አደጋዎች በሚከሰቱበት ወቅት በራሱ ለመቆጣጠር ሞክሮ ከአቅሙ በላይ ሲሆን ብቻ ለኮሚሽኑ የሚደውልበት አግባብ ሰፊ ስለመሆኑ አንስተዋል።

በመሆኑም ወዲያውኑ አደጋው እንደደረሰ በኮሚሽኑ ነፃ የስልክ መስመር 939 በመደወል አፋጣኝ ምላሽ በማግኘት በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት መቀነስ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ