መስከረም 12/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በቱሪዝም ዘርፉ ገበታ ለሀገርን ጨምሮ ልዩ ፖሊሲ ተቀርጾ መሰራቱ የሀገር ውስጥ እና የውጭ አልሚዎች በዘርፉ ኢንቨስት እንዲያደርጉ እድል ፈጥሯል ሲል የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በዘርፉ በርካታ ስራዎች መሰራቱን፤ የኮሚሽኑ የኮሙኒኬሽንና ሕዝብ ግንኙነት ቡድን መሪ አሸናፊ ሀብቴ ለአሐዱ ተናግረዋል።

በተለይም ነባር እና አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን ለሀገር ውስጥ እና ለተቀረው ዓለም የማስተዋወቅ መሰራቱን ገልጸዋል።

ይህን ተከትሎም የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን የሚጎበኙ ቱሪስቶችን ቁጥር ከማሳደግ ባለፈ ለአልሚዎች እድል መፍጠሩን ጠቁመዋል።

በአሁኑ ጊዜ አልሚዎች በቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ሆቴሎች እና ሪዞርቶች እንዲሁም በቱሪዝም ሥራ ላይ እንዲሳተፉ እድል መፍጠሩን ተናግረዋል ።

በ2018 በተለየ ሁኔታ የሚሰሩ ሥራዎች እንዳሉ ያነሱት ቡድን መሪው፤ ከእነዚህም መካከል አንዱ ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ እንዲተዋወቅ ማድረግ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተያያዘ የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን አምስተኛውን የቱሪዝም ሳምንት ከመስከረም 20 እስከ 22 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል እንደሚያስተናግድ አስታውቋል።

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ነጋ በቱሪዝም ሳምንት መርሃግብሩ በዓለም፣ በአፍሪካ፣ በሀገር አቀፍ እና በክልል ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ ድርጅቶች የቱሪዝም ምርቶቻቸውን ለኤግዚቪሽን እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል።

ከዚህም ባለፈም የቱሪዝም ፎረም ይካሄዳል የተባለ ሲሆን፤ በዚህም በቱሪዝም ዘርፍ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦች ሽልማት ይበረከታል ብለዋል።

በመርሃግብሩ ከዓለም አቀፍ የቱሪዝም ቦርድ እና ቱሪዝም አባላት መካከል ኬንያ፣ ናሚቢያ፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ኡጋንዳ እና ጅቡቲ የተውጣጡ ተሳታፊዎች ይታደማሉ ተብሏል።

በሌላ በኩል የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን በየዓመቱ የሚያካሄደውን "ሚስ ቱሪዝም ኦሮሚያ" ውድድር ዘንድሮም በተመሳሳይ በደማቅ ሥነ-ስርዓት እንደሚካሄድ ተገልጿል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ