ጥቅምት 18/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በምስራቅ አፍሪካ የአየር ንብረት ተስማሚ ግብርናን ለመደገፍ "የመሬት፣ የአፈር እና የሰብል መረጃ አገልግሎቶች" የተሰኘው ፕሮጀክት፤ ለአራት ዓመታት በኢትዮጵያ፣ በኬንያና በሩዋንዳ ሲሰራበት የቆየውን ቁልፍ ውጤቶችና የተገኙ ልምዶችን ይፋ በማድረግ ተጠናቋል።

የዚህ ፕሮግራም አላማ በሀገራዊ የምርምር ተቋማት ውስጥ ዘላቂነት ያላቸውን የመሬት፣ የአፈርና የሰብል መረጃ ማዕከላትን በማቋቋም ሀገራዊ የግብርና እውቀትና ፈጠራ ሥርዓቶችን በማጠናከር ላይ ነው።

የመረጃ ማዕከላቱ ባለፉት አራት ዓመታት የተሰበሰበው መረጃ በማቀናበርና በማስተሳሰር በማስረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ አሰጣጥን የሚያጎለብቱ ሲሆን፤
መረጃው ለባለድርሻ አካላት በቀላሉ ተደራሽ እንዲሆን ያስችላሉ ተብሏል፡፡

የመሬት፣ የአፈርና የሰብል መረጃ ማዕከላቱ የተነደፉት በሀገር አቀፍ፣ በክልልና በአካባቢ ደረጃ ያሉ የግብርና ባለድርሻ አካላትን ለማገልገል ሲሆን፤ የአየር ንብረት ተስማሚ የግብርና ልምዶችን ለመደገፍ፣ የገጠርማ አካባቢ ለውጥን ለማስፋፋት እንዲሁም የምግብ ሥርዓት ጥንካሬን ለማጠናከር የተቀናጀ መረጃን ማቅረብ ሥራ እንደሚከናወን ተነግሯል፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩቱ ፕሮጀክቱን አስመልክቶ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የፈጠርናቸው አጋሮች፣ ያስተዋወቅናቸው ፈጠራዎች እና ያካፈልነው ዕውቀት ሊቀጥሉ የሚገባቸው መልካም ሁኔታዎች ናቸው ብሏል፡፡

የኢንስቲትዩቱ የቦርድ ሰብሳቢ አበራ ደሬሳ (ዶ/ር)፤ "ለሁሉም የገንዘብ ደጋፊዎች እና ለሀገር ውስጥ አጋሮቻችን ምስጋናዬን አቀርባለሁ" ብለዋል

የአራት ዓመት የሥራ መርሃግብር በሦስት ብሔራዊ የግብርና ምርምር ተቋማት ውስጥ የመሬት፣ የአፈር እና የሰብል መረጃ የሚያቀናጁ ማዕከላትን በተሳካ ሁኔታ ገንብቶ አጠናቋል ነው ያሉት።

እነዚህም የኢትዮጵያ የግብር ምርምር ኢንስቲትዩት፣ የኬንያ ግብርናና እንስሳት እርባታ ምርምር ድርጅት እና የሩዋንዳ ግብርናና የእንስሳ ሀብት ልማት ቦርድ በሦስቱ አጋር ሀገራት ውስጥ ይገኛሉ ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የማዕከሉ ውጤቶችም፤ ማዕከል ማቋቋም፣ የተበታተነውን የምርምር መረጃ ወደ አንድ ለማሰባሰብ እና ደረጃውን የጠበቀ ለማድረግ የተነደፈ የመሬት፣ የአፈርና የሰብል መረጃ ማዕከላት መዘርጋት ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የአቅም ግንባታን በማሳደግ፤ ልዩ ሥልጠና በመስጠት የአካባቢው ሠራተኞች ውስብስብ የሆኑ የመረጃ ሥርዓቶች በራሳ አቅም የማስተዳደር እና የማስቀጠል ሙሉ ብቃት እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል።

በተጠቃሚዎች ላይ የተገኘው ለውጦች ደግሞ፤ የመሬት አስተዳደርን ለማሻሻል እና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የሚስማማ ግብርናን ለመተግበር እንዲቻል መረጃውን መጠቀም እድልን በማስፋት፤ የመጨረሻ ተጠቃሚዎችን የሀገር ውስጥ ገበሬዎችን ጨምሮ፣ በማሳተፍ ሥልጠና መሠጠቱ ተገልጿል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ