ሕዳር 16/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ሕጻናት በተለያየ መንገድ ለተለያዩ ጥቃቶች ተጋላጭ ሲሆኑ ከጊዜ ጋር እያደገ የመጡት የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በኩል ለጥቃት ተጋላጭ መሆናቸውን የአፍሪካ ቻይልድ ፓሊሲ ፎረም ገልጿል።

የአፍሪካ ቻይል ፓሊሲ ፎረም የፕሮግራም ዳይሬክተር ሽመልስ ፀጋዬ፤ ሕጻናት ያለምንም ገደብ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ መሆናቸው ለጥቃት እያጋለጣቸው እንደሚገኝ ለአሐዱ ሬዲዮ ገልጸዋል።

ሆኖም ግን በኢትዮጵያ በማህበራዊ ሚዲያ ለሚፈጸም ጥቃት ከለላ የሚሰጥ የሕግ ማዕቀፍ አለመኖሩን አንስተዋል።

በዚህም ሕጻናትና አዋቂዎች በእነዚህ ገጾች ላይ በጋራ እንዲጠቀሙ እንዲነጋገሩ እና ለአላስፈላጊ ሁነቶች እንዲጋለጡ ያደርጋል ብለዋል።

Post image

ሌሎች ሀገራት የኦንላይን ደህንነት ላይ ጠንካራ ሕጎች እንዳሏቸው የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ በዚህም በርካታ ችግሮችን መፍታት እና መቆጣጠር መቻላቸውን አንስተዋል።

በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ባላቸው ኢኮኖሚ እና ማህበራዊ መስተጋብር ላይ ከለላ የመሰጡባቸው ጥሩ ልምዶች ትምህርት መውሰድ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

ስለሆነም በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ የሕግ ክፍተቶችን መሙላት፣ የትኛው ሕግ ሕጻናትን በይበልጥ መጠበቅ ይችላል የሚለውን መመልከትና ማሻሻያዎችን ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ የማህበራዊ ጉዳዮችን በመለየት በጀትና ትኩረትን እሱ ላይ ማዋል እንደሚያስፈልግም አቶ ሽመልስ ተናግረዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ