ሕዳር 16/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ኤስ ኦ ኤስ የሕጻናት መንደሮች በኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ኤስ ኦ ኤስ የሕጻናት መንደሮች ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን የብራንድ አምባሳደርነት ሹመት በዛሬው ዕለት ለአርቲስት አለማየሁ ታደሰ ሰጥቷል፡፡
የድርጅቱ በኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን ብሄራዊ ዳይሬክተር አቶ ሣህለ ማርያም አበበ ለአሐዱ ሬዲዮ እንደተናገሩት፤ ኤስ ኦ ኤስ ለተከታታይ 51 ዓመታት በጎዳና ላይ ያሉ ሕጻናት እና ወላጆቻቸው በሞት የተነጠቁ ወጣቶችን ሲረዳና ሲንከባከብ ቆይቷል።

በዛሬው ዕለትም አርቲስት አለማየሁ ታደሰን ለሁለት ዓመት የብራንድ አምባሳደር ማድረጉ የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ አርቲስቱን የብራንድ አምባሳደርነት ሹመቱን ያለምን ክፍያ መቀበሉ በበጎ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
ኤስ ኦ ኤስ የሕጻናት መንደሮች በኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ኤስ ኦ ኤስ የሕጻናት መንደሮች 47 የሚደርሱ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን የገለጹም ሲሆን፤ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ካለፉት ዓመታት በተሻለ በሕጻናት እና ወጣቶች ላይ እንደሚሰራ አስታውቋል።
አርቲስት አለማየሁ ታደሰ የድርጅቱ ብራንድ አምባሳደር ተደርጎ ሲመረጥ ምርጫው ጥንቃቄ እና ግልፅ አሰራርን የተከተለ ነበር ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ይህም የእጩነት ምዕራፍ፣ የአስመራጭ ኮሚቴ ዝርዝር ግምገማ እና ሰፊ የሰራተኞች ተሳትፎን ያካተተ እንደነበርና ሂደቱ የተነደፈው ፍትሃዊነትን እና ከድርጅቱ እሴቶች ጋር መጣጣምን በማረጋገጥ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም መሰረት ከቀረቡት እጩዎች መካከል አርቲስት አለማየሁ ታደሰ በአቋሙ፣ ለረጅም ጊዜ በዘለቀው መልካም ስሙ፣ ለሕጻናት ደህንነት ባለው ቁርጠኝነት እና ከድርጅቱ ተልዕኮ ጋር የሚጣጣም ስብዕና ያለው ሆኖ በመገኘቱ መመረጡን ገልጸዋል።
አርቲስቱን የብራንድ አምባሳደር አድርጎ መሾሙ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ይገኝ የነበረው ድጋፍ እየቀነሰ በመምጣቱ የራስን ችግር በራስ ለመፍታት ለሚሰራው ሥራ እንደሚያግዝ ተገልጿል።
የብራንድ አምባሳደሩ ሚናም ድርጅታዊ አጋርነትን ለማስፋት፣ የገንዘብ ማሰባሰብ ጥረቶችን ለማጎልበት እና በቂ የወላጅ እንክብካቤ ሳያገኙ የሚያድጉ ሕጻናት እና ወጣቶች የበለጠ የህዝብ ትኩረት እንዲያገኙ ለማስቻል ያለመ ነው ተብሏል።
አርቲስት አለማየሁ ታደሰ በበኩሉ፤ ከኤስ ኦ ኤስ የሕጻናት መንደሮች በኢትዮጵያ ጋር ያላው ግንኙነት በሐረር የልጅነት ዘመኑ የጀመረ በመሆኑ፤ ድርጅቱ በሕጻናት እና ቤተሰብ ላይ ያሳረፈውን የረዥም ጊዜ በጎ ተፅእኖ ለመረዳት እንዳስቻለው ገልጿል።

በመሆኑም "የብራንድ አምባሳደር መሆን ከማዕረግ በላይ የሆነ እና ትከከለኛ ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ ለማበርከት የሚያበቃ ትልቅ ኃላፊነት እና እድል ነው። ባገኘሁት መድረክ ሁሉ ድምፄን ለማሰማትና የድርጅቱን ተልዕኮ ለማጉላት ሙሉ ቁርጠኝነቴን ስገልጽ ከብር ይሰማኛል" ሲል ተናግሯል።
ኤስ ኦ ኤስ የሕጻናት መንደሮች በኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ኤስ ኦ ኤስ የሕጻናት መንደሮች ችግር የሆነበት ግጭት ባለባቸው አካባቢ በሚፈልገው ልክ ተንቀሳቅሶ እየሰራ አለመሆኑን እና ድርጅቱ ለማስፋፋት የገንዘብ እጥረት መኖሩ እንደሆነ አስታውቋል።
ይህም የብራንድ አምባሳደር ስምምነት ድርጅቱ ሕዝባዊ ህላዌውን ለማጠናከር፣ የማህበረሰብ ተሳትፎን ለማጎልበት እና በመላው ኢትዮጵያ ያሉ ሕጻናትን እና ወጣቶችን የመጠበቅ እና የማብቃት ተልዕኮውን ለማጎልበት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ መሆኑን ተመላክቷል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ