መስከረም 30/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ዘመን ባንክ ከዚህ በፊት በተለያዩ ጊዜያት በገንዘብ እና በአይነት ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱ የተገለጸ ሲሆን፤ ለተመረጡ 19 ድርጅቶች 29 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የእርዳታ መርሀ ግብር አካሂዷል።
ከዚህ በተጨማሪም ለበጎ አድራጎት ድርጅቶቹ እውቅና የሠጠ ሲሆን፤ ተቋማቱ የተመረጡት ባበረከቱት አስተዋፅኦ፣ ባላቸው የእቅድ አፈፃፀም እና የወደፊት ራዕይ ላይ ተመስርቶ በተደረገ ጥናት መሠረት ነው ተብሏል።
የተመረጡት 19 ድርጅቶችን እውቅና ከመስጠት እና ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ፤ ወደፊትም አብሮ ለመስራት እቅድ መያዙን ለአሐዱ የተናገሩት የዘመን ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሮ እሌኒ ቢምር ናቸው።

ከ19ኙ ተቋማት ውስጥ 15ቱ አዲስ አበባ ውስጥ እንደሚገኙ የጠቆሙት የቦርድ ሰብሳቢዋ፤ ቀሪ 4ቱ ደግሞ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይ እና በሲዳማ ክልሎች የሚገኙ ናቸው ብለዋል።
ከድርጅቶቹ መካከል ብራይት ውመን አሶሴሽን፣ በኤች አይቪ ኤድስ መከላከል ላይ የሚሰራው ሕይወት ኢትዮጵያ፣ ሮሆቦት የምገባና የጥናት ማዕከል የሚገኙበት ሲሆን፤ እያንዳንዳቸው አንድ ሚሊየን ብር ተበርክቶላቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ክብር ለአረጋውያን፣ ቤዛ ለሕይወት፣ ቤቴል የኦቲዝም ማዕከል፣ የወደቁትን አንሱ የነዳያን በጎ አድራጎት ማህበር፣ ነህሚያ ኦቲዝም ማዕከል፣ ጌርጌሴኖን የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ማቲዎስ ወንዱ የካንሰር አሶሲየሽን እያንዳንዳቸው 1 ሚሊየን 500 ሺሕ ብር ድጋፍ ተደርጎላቸዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕጻናት መርጃ ማዕከል፣ የኢትዮጵያ ካንሰር ማህበር፣ ዲቦራ ፋውንዴሽን፣ ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያና መቄዶንያ የአረጋውያን መርጃ ማዕከል ደግሞ፤ እያንዳንዳቸው ሁለት ሚሊየን ብር ድጋፍ ተደርጎላቸዋል ሲሉ ነው የቦርድ ሰብሳቢዋ የተናገሩት፡፡
"ዘመን ባንክ ድጋፉን ያደረገው ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ነው፤ ይህም ያለውን የበጎ አድራጎት ሥራ የሚያሳይ ነው" ያሉት የቦርድ ሰብሳቢዋ፤ ባንኩ በሚደግፋቸው ዜጎች ሕይወት ላይ ጥራት መፍጠር አላማችን ነው ሲሉ ገልጸዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ